የ2015 ዓ.ም. ምረቃ መጽሔት
ማእከላት
ግቢ ጉባኤያት
ተመራቂዎች
የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡
“ወባረኮሙ ኢያሱ ወፈነዎሙ – ኢያሱም መረቃቸው፣ ሰደዳቸውም፤”(ኢያሱ ፳፪፡፮)
ክቡራንና ክቡራት የ2015 ዓ/ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ግቢ ጉባኤ ምሩቃን
ከሁሉ አስቀድመን አምላከ ቅዱሳን፣ መፍቀሬ ሊቃውንት፣ ሊቀ ካህናት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁላችሁም የሚጠበቅባችሁን ትምህርታችሁን አጠናቃችሁ ለዛሬው ድርብ የምረቃ በዓል ስላደረሳችሁ ክብር ይግባውና እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን፡፡
ምሁራነ ኦሪት ከመጻሕፈተ ኦሪት ውስጥ የታሪክ መጻሕፍት የሆኑትን በልዩ ልዩ መልኩ ያጠኗቸዋል፡፡ በዚህም ከመጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ እስከ 2ኛ ነገሥት ያሉትን መጻሕፍት “መጻሕፍተ ታሪክ ዘቀደምት ነቢያት” በማለት ይጠሯቸው ነበር። ሊቃውንቱ እነዚህን መጻሕፍት የታሪክ መዛግብት ብቻ አድርገው ሳይቆጥሩ፥ የቀደምት ነቢያትን ትምህርትና ምሳሌ የያዙ በመሆናቸው ከኦሪተ ሙሴ ሳይለዩ ያስተምሩባቸዋል፡፡ ለመጻሕፍቱ የሚሰጡት ክብር ትውልዱ ከይዘታቸው እንዲማርና በጥንቃቄ እንዲራመድ ያደርጉታል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ልጄ ሆይ በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን ይላልና (ምሳሌ 3፡7)፤ ሕዝበ እግዚአብሔር በልብ ወለድ ሐሳብ እንዳይነዳ ለመጻሕፍቱ መልእክት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ያስተምራሉ፡፡ የእምነትም ይሁን የቀኖና፣ የታሪክም ይሁን የሕግ፣ መጻሕፍት ዓላማ ትውልድ የመጻሕፍትን መልእክት ባለማወቁ ምክንያት እንዳይፈረድበት፣ ጥፋት እንዳያገኝው በማስረጃ ለመምከር ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሰው የመስፍን ኢያሱ መጽሐፍም ከሚያስተላልፈው መልእክት ውስጥ አንዱ በጠላቶች ላይ ድል የሚያገኘው በእግዚአብሔር ኃይልና ጥበብ ብቻ መሆኑን በጥብቅ ያስገነዝባል። የእግዚአብሔር ሕዝብ በአምላካቸው ላይ በፍጹም እምነት በሚደገፉበት ጊዜ አሸናፊ እንደሚሆኑ እርሱን ሲታዘዙ ድል አድራጊነታቸው እንደሚጨምር የመታዘዝን እና የእምነትን ኃይል በሚገባ ያስተምራል፡፡
መስፍን ኢያሱ የተስፋ ምድር የሆነቸውን ከነዓንን ለሕዝበ እስራኤል ካካፈላቸው በኋላ ሁሉም በየተመደቡበት ተጓዙ፤ በማኅበራዊም ሆነ በሥርዓተ አምልኮ ጊዜ ሊፈጽሙት የሚገባቸውን ሁሉ አደረጉ፤ በመካከል የነበረውንም ልዩነት በፍትሕ፣ በምክክር እና በስምምነት ጨረሱ ከዚያ በኋላ ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ “የእግዚአብሔር ባለሟል ሊቀ ነቢያት ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፣ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፤ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፣ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። አሁን እንግዲህ ተመለሱ፣ ወደ ቤታችሁና የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፣ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወዱ ዘንድ፣ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፣ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጠጉ ዘንድ፣ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ ብሎ መረቃቸው፣ ሰደዳቸውም፡፡ እነሱም በሰላም ወደ ቤታቸው ሄዱ።”
የተከበራችሁ በዓለማዊው ዕውቀት የላቃችሁ መንፈሳዊ ትምህርት የቀሰማችሁ የግቢ ጉባኤ ምሩቃን
እንደሚታወቀው የተጻፈው ሁሉ ለእኛ ምክር፣ ተግሣጽና ትምህርት እንዲሆን የተጻፈ ነው፡፡ ኢያሱ ሕዝብን እንዲመራ፣ ወደ ተስፋው ምድር እንዲያስገባ የተመረጠ፣ የመላውን ሕዝብ ደኅንነት ጠብቆ፣ ከነገድ ነገድ ሳያዳላ፣ ከእውነተኛ መሪ በሚጠበቅ መልኩ ሁሉንም በአንድነት መርቶ ከነዓን አስገባ፤ ርስትንም አካፈለ፣ ከዚያም አስደናቂ የሆነ ምርቃትን አስተላለፈ፣ የኢያሱ ምርቃት ቡራኬን ከምዕዳን ጋር ያስተባበረ ሰማያዊ ጸጋን የሚያሰጥ ምድራዊ ሕይወትን የሚያስተካክል መመሪያ ነው፡፡
በመጀመሪያ ለምርቃት የበቃው ሕዝብ ከኢያሱ በፊት የነበሩ የአባቶቹን ትእዛዝ የጠበቀ ትውልድ መሆኑንን “የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል” በማለት አረጋገጠ፣ በመቀጠልም “እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል” በማለት በዘመኑ ለተሠየመው ፍትሐዊና ብልህ፣ አድሎ የሌለው ለሁሉም እኩል የሚያገለግል፣ ለሕዘቡ ደኅንነት ራሱን አሳልፎ ለሚሰጠው መሪያቸው መታዘዛቸውን አሳወቀ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በነገድ በቤተሰብ ሳይለዩ ወገኖቻቸውን መርዳታቸውን “ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም” ብሎ ፍቅረ ቢጽ ያላቸው መሆኑን መሰከረ፤ በመጨረሻ በዐራተኛ ደረጃ “የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል” ብሎ። ለፈጣሪ ሕግ መገዛታቸውን አረጋገጠላቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ባረካቸው፣ መረቃቸው፣ ያለነቀፌታና ያለፍርሃት በሰላም አሰናበታቸው፡፡ ከመረቃቸው እና ከባረካቸው በኋላም ከላይ የተጠቀሱትን ዐራት ትእዛዝት ማለትም ሕገ አበውን፣ ሕገ ዘመንን፣ ፍቅረ ቢጽን፣ ፍቅረ እግዚአብሔርን ጠብቁ ብሎ አዘዛቸው፡፡ ይህን ያደረገበት ምክንያት ምርቃቱና ቡራኬው የሚጸናው ለቡራኬ ምክንያት የሆነንን መሥፈርት ጠብቀን ስንገኝ መሆኑን በጥብቅ ለማስገንዘብ፣ እስከ መመረቅ ያደረሰንን ዕሴት ከምረቃ በኋላም መጠበቅ እንዳለብን ለማሳሰብ ነው፡፡
ለመመረቅ ከተጋን ዘንድ የተመረቅንበትን ምክንያት ለመጠበቅ የበለጠ መትጋት ይገባል፤ ለመመረቅ የጓጓነውን ያህል በተመረቅንበት ጠንክረን ለመሥራት መትጋትን ልንጓጓ ይገባል፡፡ አለበለዚያ ምርቃቱና ቡራኬው እስከ ምረቃው ቀን ድረስ ብቻ ይሆነናል፡፡
ቡሩካንና ቡሩካት የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፣ የቤተ ክርስቲያናችን የቁርጥ ቀን ባለሟሎች!
ነቢይ ኢያሱ ተናገራቸው ዐራት ትእዛዛት ዛሬም የምረቃ መስፈርት ናቸው፤ አሁንም አሉ፣ እነርሱም አንደኛ የአባቶቻችንን ትውፊት እና ባህለ አእምሮ፣ ዕቅበተ እምነት፣ መጠበቅ ዋናው ነው፤ ሁለተኛው በዘመናችን ያለው ትውልድ የደረሰበትን ደረጃ አልፈን ጥያቄውን መልሰን፣ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ጥቃት አክሽፈን የሃይማኖት ርስትን የመጠበቅ ግዴታ ነው፤ ሦስተኛው በዘመን አመጣሽ የክፍፍል ሤራ ሳንሸነፍ፣ ሁላችንም በክርስቲያናዊ ቤተሰብ አንድ መሆናችንን በማመን እና በተግባር በመግለጽ ለወገኖቻችን ያለንን ቀና አገልግሎት መግለጽ፣ መደጋገፍ እና መተባባርን ይመለከታል፤ በመጨረሻም በዘመን የማይለወጠው ፍቅረ እግዚአብሔር እና ፍቅረ ሃይማኖት ናቸው፡፡
ቡሩካንና ቡሩካት!
እናንተን ከሌሎች ምሩቃን ሁሉ ልዩ የሚያደርጋቸሁ ድርብ ተመራቂ መሆናችሁ ነው፤ በዩኒቨርስቲ ቆይታችሁ በርካታ ሙያዎችን በጽንሰ ሐሳብ እና በቤተ ሙከራ ተምራችሁ በየሙያችሁ ተመርቃችኋል፣ በተጨማሪም ባላችሁ ትርፍ ጊዜ ዋዛ ፈዛዛን ሳትከተሉ፤ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ቁጭ ብላችሁ የተዘጋጀላችሁን መንፈሳዊ ትምህርት ቀስማችሁ ሁለተኛውን ምረቃ ደግሞ ከእግዚአብሔር ቤት ተመረቃችሁ፡፡
እንግዲህ እናንተ ብዙ ተሰጥቷችኋል እና ብዙ ይጠበቅባችኋል፤ የእኛ ዘመን ትውልድ ብዙ ችግር አለበት ካልን ብዙ መፍትሔ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደእናንተ ያሉ በሁለት ወገን የተመረቁ ወጣቶች ያስፈልጉናል፡፡ ስለዚህ በተማራችሁ ትምህርት እና በሰለጠናችሁበት ሙያ ሀገራችሁን፣ ቅድስት እናት ቤተ ክርስቲያናችሁን እና ሕዝባችሁን በትጋት እና በቅንነት እንድታገለግሉ፣ ለችግሩ መፍትሔ፣ ለድካሙ ጥንካሬ እንድትሆኑ አደራ በማለት ሁላችሁንም የዛሬ ምሩቃን እንኳን ደስ አላችሁ፣ እግዚአብሔር አምላካችን የሥራና የአገልግሎት ዘመናችሁንና ሕይወታችሁን በሙሉ ይባርክላችሁ ይቀድሳችሁ እላለሁ፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን
ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለዓለም ሁሉ ሰላምን ይስጥ!
አባ አብርሃም
የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ መንበረ ፓትርያርክ
ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና
የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ሰኔ 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ
“መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” (፪ጴጥ.፩÷፲)
የተከበራችሁ ውድ የግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎቻችን እንኳን ደስ ያለችሁ!!!
“ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ” እንዲል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በግቢ ጉባኤ ቆይታችሁ ገበሬ በክረምት እንደሚደክም፣ ውጣ ውረዱ እንደሚበዛበት ሁሉ እናንተም ሁሉን ተቋቁማችሁ በዕውቀት፣ በሃይማኖት በምግባር ጸንታችሁ የልፋታችሁን ዋጋ አግኝታችሁ ለመመረቅ በቅታችኋልና እንኳን ደስ ያላችሁ!!!
መመረቃችሁ የሚያስመሰግን ቢሆንም ገና የሕወይትን ጣዕም የምትቀምሱበት፣ አጣጥማችሁም ጣፋጩን ከመራራው የምትለዩበት ጊዜ ደርሷልና ራሳችሁን የምታዘጋጁበት መሸጋገሪያ ምዕራፍ ላይ ትገኛላችሁ፡፡ በግቢ ጉባኤያት ውስጥ ጽድቁንና መንግሥቱን ትሹ ዘንድ መንፈሳዊውን ዕውቀት እየተመገባችሁ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከማወቅ አልፋችሁ በመንፈሳዊ ሕይወት በጾም፣ በጸሎት፣ በምግባር ጸንታችሁ ቆይታችኋል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ ባወቃችኋት ቁጥርም ሥርዓቷን መጠበቅ፣ በመንገዷም መመላለስ፣ ለሌሎችም አርአያ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡
በግቢ ጉባኤያት ቆይታችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችሁ የመገበቻችሁ መንፈሳዊ ምግብ ስንቅ ሆኗችሁ በአባቶች ቡራኬ ተመርቃችሁ ስትወጡም በያላችሁበት እንደተሰጣችሁ ጸጋ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ማገልገልና መገልገል እንደ መሠረታዊ ተግባራችሁ በመቁጠር መበርታት ከእናንተ ይጠበቃል፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤት፣ በሰበካ ጉባኤ፣ በማኅበራት፣ እንዲሁም በማኅበረ ቅዱሳን መዋቅር ውስጥ በመሳተፍ ቅድስት ቤተ ክርሰቲያን የሰጠቻችሁን አደራ መወጣትን አለባችሁ ፡፡ ስለዚህ ከትምህርት ገበታ ወደ ሥራ ስትመጡ ባላችሁ ጊዜ ሁሉንም በሥርዓትና በአግባቡ መፈጸም ያስፈልጋል፡፡
ለቤተ ክርስቲያንም ከምታገኙት ከአሥር አንድ ዐሥራት ማውጣት ሥርዓቷን ለሚያውቅ ለአንድ ክርስቲያን ግዴታው እንደሆነ በመረዳት ተግባራዊ ማድረግም ይገባል፡፡ይህም እግዚአብሔር ራሱ ካለን ላይ ከአሥር አንድ ማውጣት እንደሚገባን በነቢዩ ሚልክያስ ላይ አድሮ ሲነግረን “ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን? እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል፤ እናንተም በምንድር ነው ብላችኋል፤ በዐሥራት እና በኩራት ነው” (ሚል.፫÷፰) እንዲል፡፡
በተሠማራችሁበት የሥራ ቦታና መስክም የቤተ ክርሰቲያንን መብት በማስጠበቅ ለሌሎች አርአያ መሆን፣ በምግባር የታነጻችሁ፣ በሃይማኖት ለእውነትና ለፍትህ የቆማችሁ እንድትሆኑ፤ የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅድላችሁ መሠረት መሳተፍ፣ ሀገራችሁንና ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል ከእናንተ ይጠበቃል፡፡
ከምረቃ በኋላ ዓለም በሯን ከፍታ ስለምትጠብቃችሁ ክፉውንና በጎውን በሃይማኖት መነጽርነት ተመልክታችሁ ሕይወታችሁ ክርስቲያን ክርስቲያን ሊሸት ይገባዋል፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችሁ በጎደለው በኩል በመቆም ችግር ፈቺ አገልግሎት እንድታገለግሉ ትፈልጋለች፡፡ ግቢ ጉባኤ ተምሬያለሁ ማለት ብቻ የሚያጸድቅ ሳይሆን ሕይወታችሁን በንስሓ፣ በጾም በጸሎት፣ በስግደት፣ በአጠቃላይ የመንፈስ ፍሬዎችን ማፍራት፣ ራስንም ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ይጠይቃልና በዚህ በኩል ንቁ ተሳታፊ ሆናችሁ መገኘት ይገባል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የምታስፈጸምና የሚፈጽሙ ምእመናን ባለቤት ናት፡፡ በክርስቲያኖች ዘንድ መከፋፈልን የሚዘራ እርሱ ከእግዚአብሔር አይደለም፡፡ በዘር፣ በጎሣ፣ በቋንቋ እና በመሳሰሉት እንከፋፈል ዘንድ አልተፈጠርንም፡። ሁላችንም የልዑል እግዚአብሔር የእጅ ሥራ ውጤቶች ነንና በክርሰቲያኖች ዘንድ መከፋፈል ከሁሉ በላይ የተጠላች ናት፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መከፋፈል እንደማይገባ ሲገልጽ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፣ እኔ የኬፋ ነኝ፣ እኔ የክርሰቶስ ነኝ፤ የምትሉትን እነግራችኋለሁ፤ ክርስቶስ ተከፍሏልን?” በማለት የቆሮንቶሳውያንን መከፋፈልን በተመለከተ ገስጿቸዋል፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ ሁላችን አንድ አካል ነንና ከዘረኝነት አስተሳሰብ መጽዳት ያስፈልጋል፡፡
ወቅቱ አንድነታችንን የምናጠነክርበትና ከውስጥም ከውጪም ቤተ ክርስቲያንን እየፈተኗት ከሚገኙ ተግባራት መራቅና ስለ ቤተ ክርስቲያን አንድነት የምንቆምበት፣ የምንተጋበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከፈተና የራቀችበት ጊዜ ባይኖርም ጠባቂዋ ክርሰቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን አይተዋትም፡፡ መርከቧ በማዕበል እንደምትናወጥ ሁሉ በርእዮተ ዓለማዊ እና መዋቅራዊ አደረጃጀት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማዋን፣ ቀኖናዋን፣ ሥርዓቷንና ትውፊቷን ለማጥፋት ዓለም እየተጋ ይገኛል፡፡ ይህንን መመከት የምንችለው በአንድነት ስንቆም ነውና ከተመራቂዎች ብዙ ይጠበቃል፡፡ ከስሜታዊነት ወጥቶ በሰከነ መንፈስ ቤተ ክርሰቲያን የገጠማትን፣ ወደፊትም ሊገጥማት የሚችለውን ፈተና በመረዳት መፍትሔ የሚፈልግና የሚያስፈጽም ትውልድ ሆኖ መገኘት ይገባል፡፡ ሁል ጊዜም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጎን መቆምም ያስፈልጋል፡፡
ሀገር ያቀናች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በየቦታው የምትቃጠልበት፣ ልጆቿም ኦርቶዶክሳውያን በመሆናቸው ብቻ የሚታረዱበትና የሚሰደዱበት ወቅት በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ለመታደግ መሥራት ከግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ይጠበቃል፡፡ በዚህ ረገድም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች በመገዛት ቅድስት ቤተ ክርሰቲያንን ካንዣበባት አደጋ መታደግ፣ የበኩላችሁንም ድርሻ መወጣት ይጠበቅባችኋል፡፡
መመረቃችሁ የስኬት ማማ ላይ መድረሳችሁን አያሳይምና በሰከነ መንፈስ ፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ምግባርን ተጫምታችሁ ሕይወታችሁን መምራት የምትጀመሩበት መንደርደሪያ ጊዜአችሁ ላይ ትገኛለችሁ፡፡ ለጊዜ ያላችሁን አስተሳሰብ በማስተካከል ሁሉንም በጊዜው እና በሥርዓት ማከናወን፣ ሀገር እና ቤተ ክርስቲያንም የሚፈልጉባችሁን የድርሻችሁን እየተወጣችሁ ዘወትር መትጋት ከእናንተ ይጠበቃል፡፡
በአጠቃላይ በጊዜው ሁሉን ያከናወነ እግዚአብሔር ነውና የተሰጣችሁን የአገልግሎት ዘመን በሃይማኖት፣ በጥበብና በፍቅር ሆናችሁ ትጠቀሙበት ዘንድ መንገድ መጀመራችሁን በመረዳት ለሀገርም ለቤተ ክርስቲያንም የምትጠቅሙ ሆናችሁ ተገኙ፡፡ “መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” (፪ጴጥ. ፩÷፲) እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን የአገልግሎት ዕድል ትጠቀሙበት ዘንድ በማሳሰብ ማኅበራችሁ ማኅበረ ቅዱሳን መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡