የ2016 ዓ.ም. ምረቃ መጽሔት
ማእከላት
ግቢ ጉባኤያት
ተመራቂዎች
“ወንድሞች ሆይ እናንተ ሁል ጊዜ ሥራ መሥራትን ቸል አትበሉ፡፡” (ተሰ. 2፥13)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“ወንድሞች ሆይ እናንተ ሁል ጊዜ ሥራ መሥራትን ቸል አትበሉ፡፡” (ተሰ. 2፥13)
ውድ ተመራቂዎች ከብዙ ዓመታት ልፋት በኋላ የድካማችሁን ፍሬ ለምትሰበስቡበት ለዚህች ዕለት ልዑል እግዚአብሔር እንኳን በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ በማለት ማኅበረ ቅዱሳን መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡ ያለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት በሰው አቅም ለማለፍ የማይታሰቡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በቅዱሳኑ ምልጃ እና ጸሎት ያለፍናቸው እንደሆኑ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በሀገራችን የተከሰቱ የጦርነት፣ የሞት፣ የመፈናቀል፣ የንብረት ውድመት፣ እና ይህንን ተከትሎ የተከሰቱት ማኅበራዊ ቀውሶች፣ በተለያዩ ቦታዎች የተከሰተው ድርቅ እና ድርቁ ያስከተለው ረኀብ፣ ማቆሚያ ያጣው የኑሮ ውድነት፣ በየጊዜው የሚከሰቱ ሰብአዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቡናዊ ቀውሶች በሀገራችንና በቤተ ክርስቲያን ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው፡፡
በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ብሔርንና ቋንቋን መሠረት በማድረግ እዚህም እዚያም የተካሔዱ ከክርስቶስ የወይን ግንድ የተቆረጡ ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመቶች እና ሹመቶቹን ተከትሎ በየቦታው የቀጠሉ የመንበር መመሥረቶች ተከስተዋል፡፡ በዚህ ሕገ ወጥነት ምክንያት የሚከሰቱ የወንድማማቾች ግጭት፣ ሞት እና ስደት ሁሉ በእነዚህ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ ሀገራችን ያየናቸው ሀገራዊ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች ለመማር ማስተማሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ የነበራቸው ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህን ችግሮች አልፎ ለዚህ የምረቃ ክብር መብቃት የሚቻለው በእግዚአብሔር ቸርነት ብቻ ስለሆነ ዘወትር እግዚአብሔርን ማመስገን፣ በቅዱሳን ምልጃ መተማመን በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና አግኝቶ ከተመሠረተ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በሓላፊነት የተሰጡትን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤያት የማስተባበር፣ የማስተማር እና በመጨረሻም በአባቶች ቡራኬ በአደራ መስቀል የማስመረቅ አገልግሎቱን በቀጣይነት እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ በያዝነው ዓመትም ማኅበሩ ተቋማዊ ለውጥ ጥናት በማድረግ “ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ የመሪነት ሚናዋን ስትወጣ ማየት” የሚል ርእይ አዘጋጅቶ እና ይህንን እውን ለማድረግ የሚያስችል ተልእኮ እና ዓላማዎች በማዘጋጀት ትግበራ ምዕራፍ ላይ ነው፡፡
በተቋማዊ ለውጡ ውስጥ ማኅበሩ በግቢ ጉባኤያት ላይ ለውጥ ለማምጣት ከሚሠራቸው ሥራዎች ውስጥ ምሩቃን በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲሁም በየደረጃው በአገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳታፊ እና የመሪነት ሚናቸውን የሚወጡ እንዲሆኑ የማብቃት አገልግሎቱን ያከናውናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኦርቶዶክሳውያን ምሩቃን የማያምኑትንና የጠፉትን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደ ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መመለስ፤ በንግግራቸውና በተግባራቸው ኦርቶክሳዊነት ሊመሰክሩ የሚችሉ ኦርቶዶክሳዊ ምሩቃንን ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ ልዩ ፍላጎት ወይም ተሠጥኦ ያላቸው፤ የሚዲያ፣ የኪነ ጥበብ፣ የማኅበረሰብ አንቂ እና ሌሎችም ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ምሩቃን ቤተ ክርስቲያንን በአግባቡ የተረዱ እና ይህንንም በተግባር የሚገልጹ፣ አርአያ ክህነትን የጠበቁ፣ በየሙያ መስካቸው እና ዝንባሌያቸው ውጤታማ የሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ምሩቃንን ማፍራት ነው፡፡
ስለሆነም ይህንን የማኅበሩን ርእይ እውን ለማድረግ እና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂዎች ማምጣት የፈለገው ውጤት በእናንተ ሕይወት ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ እና ከላይ የተዘረዘሩ ችግሮችን ለመፍታት የመፍትሔው አካል ከመሆን አንጻር ከእናንተ ከምሩቃን ብዙ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ከምረቃ በኋላም “ወንድሞች ሆይ እናንተ ሁል ጊዜ ሥራ መሥራትን ቸል አትበሉ፡፡” (2ኛተሰ. 3፥13) እንዳለው ሐዋርያው አገልግሎታችሁን በመቀጠል የሚከተሉትን ተግባራት ታከናውኑ ዘንድ እንጠብቃለን፡-
በመጨረሻም ከምረቃ በኃላ ወደ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለመግባት በምታደርጉት በማንኛውም እንቅስቃሴ ማኅበረ ቅዱሳን ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች እያሳወቅን በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገራት በአገልግሎት ለመሳተፍ የማኅበሩን መዋቅር ከግንኙነት ጣቢያ እስከ ዋናው ማእከል ከጎናችሁ ስለማይለይ ቀርባችሁ እንድትጠይቁ ማስታወስ እንወዳለን፡፡ ለዚህ ሁሉ የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን ጸሎት አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን፡፡