ፈተና 

 

                                ክፍል  ሁለት

                     መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ስንታየሁ አባተ (አውስትራልያ)

ፈተና ለምን?

ፈተና ከዬትም አቅጣጫና አካባቢ ወይም ምክንያት ይምጣ በውስጡ ግን ዓላማ ይኖረዋል። ትልቁ ነገር የፈተናው መምጣት ሳይሆን ለፈተናው ዓላማ ዝግጁና ብቁ ኾኖ መገኘቱ ላይ ነው።

 1. ፈተና የኃጢአታችን ውጤት ሊኾን ይችላል:: ምክንያቱም ሰው የዘራውን ያጭዳልና።
 2. ፈተና ሊቀሰቅሰንና ሊያተጋን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚተላለፍልን ደወል ሊኾን ይችላል።
 3. እምነታችንና ፍቅራችን ሊመዘንበት ሊሰጠን ይችላል።
 4. በፈተና ለተያዙ በኃጢአት ለወደቁ መራራትን እንድንማር ሊሰጠን ይችላል።
 5. ዋጋችንን ሊያበዛልን ልንፈተን እንችላለን።
 6. በእኛ መፈተን ውስጥ ሌሎችን ሊያስተምርበት ሊሰጠን ይችላል።

ከላይ ለመግለጥ እንደተሞከረው የፈተና ምክንያቱ በርካታ ነው። ዋናው ነገር እግዚአብሔር ልጆቹን እንደማይፈትንና ከአቅማችን በላይ ለኾነ ፈተና አሳልፎ እንደማይሰጠን ይልቁንም ከፈተናው ጋር መውጫውን አብሮ እንደሚሰጠን መረዳትና ማመናችን ነው።

ይኽም በቅዱሳት መጻሕፍት “ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።”(ያዕ. ፩፥፲፫) እንዲሁም ““ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል” ተብሏል።( ፩ኛ.ቆሮ.፲፥፲፫)

ሊቁ ቅዱስ ባስልዮስ እንደተናገረው እግዚአብሔር የሰውን ድካም ያውቃል። ስለሚያውቅም ከአቅማችን በላይ በኾነ ፈተና እንድንወድቅበት አይሻም። ስለዚህ በእኛ ስሕተት ሳይሆን ከአእምሯችን ውጪ የኾነ ፈተና ሲገጥመን ተስፋ ልንቆርጥና ታዳጊ እንደሌላቸው ወገኖች ልንኾን አይገባንም። እርሱ ቅዱስ ጳውሎስ “በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤ አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።

እርሱም ይህን ከሚያህል ሞት አዳነን፥ ያድነንማል፤ እናንተም ደግሞ ስለ እኛ እየጸለያችሁ አብራችሁ ስትረዱን፥ በብዙ ሰዎች በኩል ስለ ተሰጠን ስለ ጸጋ ስጦታ ብዙዎች ስለ እኛ ያመሰግኑ ዘንድ፥ ወደ ፊት ደግሞ እንዲያድን በእርሱ ተስፋ አድርገናል” በማለት እንዳስተማረን የሞት ጥላ ቢከብበን እንኳን ከፈተናው ያድነናል (፪ኛ ቆሮ.፩:፰-፲፩)

ፈተና ሲገጥመን ምን እናድርግ ?

ፈተናን በሥጋዊ ጥበብ ማሸነፍ አይቻልም። በመኾኑም እንደ ኦርቶዶክሳዊነታችን ፈተና ሲገጥመን ፈተናውን በምን ዓይነት መንፈሳዊ ጥበብ መፍታት እንዳለብን ተረጋግተን ማሰብ ይጠበቅብናል።

 1. መጸለይ

ጸሎት ከፈተና ያወጣናል። ወደ ፈተናም እንዳንገባ ይጠብቀናል። ስለዚህ በወንጌል “አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን: ከክፉ ኹሉ አድነን እንጂ” ብላችሁ ጸልዩ እንደተባለው ተግቶ መጸለይ ይገባል።  በሌላ አንቀጽም ጌታችን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” ብሎ እንዳስተማረን ከፈተና በፊትም ኾነ ፈተና ውስጥ ሳለን አጥብቀን መጸለይ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ግዴታችንም ጭምር ነው።

 1. እግዚአብሔርን ማመስገን

መጽሐፍ በኹሉ አመስግኑ እንዳለን በፈተናችንም እግዚአብሔርን ልናመሰግን ይገባናል። “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና” እንዲል።( ፩ኛ ተሰ.፭፥፲፯-፲፰) ጻድቁ ኢዮብ ሰውነቱን ሀብቱንና አስር ልጆቹን በአንዲት ቀን ባጣበት ወቅት “እግዚአብሔር ሰጠ: እግዚአብሔር ነሣ:: እግዚአብሔር ይመስገን” አለ እንጂ በአፉ የስንፍናን ነገር አልተናገረም። እስቲ እኛስ እንዳናመሰግን የሚያግዱንን ፈተናዎቻችንን ከኢዮብ ፈተና አንፃር እንመዝናቸው።

 1. መጽናት

ፈተና የሚጸናው እንዲጸና ሥጋዊ ፈቃዱን የሚከተለውም ምርጫውን እንዲከተል የሚመጣበት ጊዜ አለ። በፈተና ትእግስታችን ይለካል። በፈተና እምነታችን ይመዘናል። በፈተና ፍሬውና እንክርዳዱ ይለያል። በፈተና ልዩ የእግዚአብሔር ጸጋና በረከት ይገኛል። መፍትሐው በእምነት ልብን አበርትቶ መጽናት ብቻ ነው። ቅዱስ ያዕቆብ “በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና” ያለውን በፈተና መጽናት የሚያስገኘውን በረከት ያስረዳል (ያዕ.፩፥፲፪)

ቅዱስ ጳውሎስም በፈተና የመታገስን ጥቅም “ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ ፭፥፫)   ቅዱስ ያዕቆብም በበኩሉ “ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት” በማለት በፈተናችን ውስጥ እየጸናንና እየተጽናናን መታገስ እንዳለብን መክሮናል (ያዕ.፩፥፪-፫)

 1. ንስሐ መግባት

እግዚአብሔር  ስንረሳው ነፍሳችን በኃጢአት ስትጎሰቁልና ስትሞት ጽድቅ ጠፍቶ ሁሉም በበደል ተገርኝቶ ሲያዝ የራቀውን ሊያቀርብ: የወደቀውን ሊያነሣ: የተፍገመገመውን ሊያጸና  ይገሥጸናል።ለዚኽ መፍትሄው ምክንያት ሳያበዙ ንስሐ መግባት ብቻ ነው።እኛ በንስሐ ወደ ፈጣሪያችን ስንመለስ እርሱ ደግሞ በምሕረቱ ወደ እኛ ይመለሳል።

 1. ካለፈው ልምድ መቅሰም

አንዳንድ ጊዜ እንደግለሰብም እንደቤተ ክርስቲያንም አለያም እንደ ሀገርም መሥራት የሚገባንን ባለመሥራታችን: ኃላፊነታችንን በጊዜው ባለመወጣታችን: ስንፍናን በማብዛታችን: አሠራራችንን ለፈተና ተጋላጭ በማድረጋችን ከግለሰብ እስከ ቤተ ክርስቲያንና እስከ ሀገር ልንፈተን እንችላለን የሚለው ነው።አሁን ያገኘንን ፈተና በንስሐና በእንባ ብንመልሰውም መዘጋጀትና መሥራት በሚገባን ልክ ኾነን ካልተገኘን ድጋሚ በፈተና መያዛችን አይቀሬ ነው። ያ ደግሞ እጅግ አደገኛ ነገር ነው።

ስለዚህ ከእያንዳንዱ ፈተናችን ትምህርት ልንወስድና በርትተን ልንሠራ ይጠበቅብናል።በአሁኑ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውና የበርካታ ምእመናንን ሕይወት የቀጠፈው ፈተና ለቤተ ክርስቲያናችን አዲሷ ባይሆንም ካለፉት ፈተናዎቻችን ተምረን መሥራት ማደራጀት ማሠልጠን ማንቃት መጠበቅ በሚገባን ልክ ሆነን ስላልተገኘን ነው። በመኾኑም ወጣቶች እንደሚያገሳ አንበሳ ሊውጠን በሚያደባብን ፈተና ሳይረበሹ እያንዳንዷን ፈተና ለመልካም አጋጣሚና ዕድል በመቀየር ራሳችንና ቤተ ክርስቲያናችንን ለሚመጣው ትውልድ ማሸጋገር ይጠበቅብናል።ለዚኽ ደግሞ የአምላካችን ቸርነት የድንግል ማርያም ተራዳኢነት  አይለየን።

ፈተና

 መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ስንታየሁ አባተ (አውስትራልያ)

                    ክፍል  አንድ

ፈተና በሕይወት ዘመናችን በቤተ ክርስቲያናችን እምነት ሥርዓት ቀኖናና ትውፊት መሠረት በምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞና እንቅስቃሴ ውስጥ ያለ ጥፋታችን ከተለያዩ አካላት የሚገጥመን መሰናክል እንቅፋት መከራ ስደት ወይም በሂደት ሊጎዳንና ሊያሰናክለን የሚችል አሁን ግን መልካም መስሎ የሚታየን ነገር ሊሆን ይችላል። በቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ መሠረት ፈተና ከሦስት ታላላቅ ምንጮች ሊመጣብን ይችላል።

 1. ከራሳችን

በተለያዩ የስሜት ሕዋሳቶቻችን በኩል ወደ ልባችን የሚገቡና እንደ እግዚአብሔር  ፈቃድ ያልኾኑ ወይም በቅዱሳት መጻሕፍት ከተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ የተለዩ አሳቦች በሂደት ወደ ምኞት ያድጋሉ። በምኞት የሚጀምረው ፈተና በተግባር ሲፈጸም ደግሞ ኃጢአት ይሆናል። ይኽንን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ”ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” ብሏል  (ያዕ. ፩:፲፫-፲፭)

ጠቢቡ ሰሎሞንም በምሳሌው ” የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፥ ልቡም በእግዚአብሔር ላይ ይቈጣል” ብሎ በስንፍና የምንያዝበት የአሳብና የምኞት መንገዳችን በሂደት የሚያስከትለውን መዘዝ አስረድቷል። (ምሳ. ፲፱፥፫) ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገዛ የስሜት ሕዋሳቶቻችን ፈተና የሚያመጡብን መኾናቸውን ““ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል” ብሏል (ማቴ.፲፥፴፮ )

በዚህ መሠረት በአንደበታቸው የማይገባ ነገር ተናግረው: በዐይናቸው መጥፎ ነገር አይተው: በጆሯቸው ክፉ ምክርና ወሬ ሰምተው: በሐፀ ዝሙት ተነድፈው በእጃቸው ወንጀል ሠርተው በእግራቸውም የኃጢአት ወጥመድ ወደ ተጠመደበት ተራምደው ሄደው በነፍስ በሥጋ ታላቅ ጉዳት ላደረሰባቸው ፈተና የተዳረጉ ወገኖቻችን በርካቶች ናቸው።

 1. በዙርያችን ካለው ማኅበረሰብ

ሰው ማኅበራዊ ፍጡር ነው። ቅድስት ኦሪት “ለሰው ብቻውን መኖር አይገባም” እንዳለችው በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የምንኖረው ከሌሎች ጋር ነው። በምንኖርበት በምንሠራበት በምንጓዝበት በመሳሰሉት ኹሉ በእምነት በባህል በአመለካከት በዕድሜ በጾታና በመሳሰሉት ሁሉ ከተለያዩ ሕዝብ ጋር እንገናኛለን። በዚህ አብሮነት ደግሞ የእውቀት የልምድ የአመለካከት ልውውጥ ይከሰታል። ደካማው በብርቱዎቹ ተጽዕኖ ይደረግበታል። በደካማነቱ እምነታቸውን ባህላቸውን ክህደታቸውን ሥጋዊ ፈቃዳቸውን ይጭኑበታል። በዚህም ጌታችን በእሾህ መካከል የወደቀ ዘር ብሎ እንዳስተማረው መልካም ክርስትናውን ከግራ ከቀኝ ያስጨንቁበትና ያለ ፍሬ እንዲቀር ያደርጉታል።

የሔዋን ምክንያተ ስሕተት መኾን: ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይኾናል። ቅዱስ ጳውሎስም “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ያለው ፈተና በዙርያችን ካሉና ከፈቃደ እግዚአብሔር ካፈነገጡ ሰዎች ስለሚመጣ ነው። (፩ኛ ቆሮ.፲፭፥፴፫) ስለኾነም ነው ክቡር ዳዊት  “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” በማለት  ያስረዳው።(መዝ.፩፥፩ )

በክፉዎች ምክር የሚሄድ በኃጢአተኞች መንገድ (አሳብ ምክር) የሚሄድ በዋዘኞች ወንበር የሚቀመጥ (ድርጊት የሚተባበር) ለፈተና የተዳረገ ይኾናል። ይኸው ክቡር ዳዊት በሌላኛው መዝሙሩ ይኽንን አሳቡን ሰፋ አድርጎ “ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ” በማለት በዙርያችን ካሉት ሰዎች የተነሣ የሚገኘውን በረከትና የሚመጣብንን ፈተና አስረድቷል። (መዝ.፲፯:፳፭)

 1. ከሰይጣን

ሰይጣን ሥራው መፈታተን: ማዘግየት: ማሰናከልና መክሰስ ነው። ይኽ የማያቋርጥና ተስፋ የማይቆርጥ ባላጋራ ምእመናን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዲክዱ አንድነታቸውን እንዲያፈርሱ ምግባር ትሩፋታቸውን እንዲተዉ ንጽህናቸውን እንዲያረክሱ በክፉ ድርጊት ፈጣሪያቸውን እንዲያስቆጡ ተስፋ እንዲቆርጡ ይፈታተናቸዋል። ምክንያቱም እርሱ ፈታኝና መፈታተንም ሥራው ስለኾነ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ የዚኽን ጨካኝ ባላጋራ መፈታተንን “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” እያለ አስተምሮናል።

ፈታኝ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን በክፉ ምክሩ ከገነት አስወጥቷል። ቃየል ወንድሙ አቤልን እንዲገድለው መግደልን አስተምሯል። በበለዓም አድሮ እስራኤል የሚጠፉበትን ለባላቅ አስመክሯል። በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ኢዮብን ከስሷል። በምናሴ አድሮ ነቢየ ልዑል ኢሳይያስን በመጋዝ አሰንጥቋል።በሄሮድስ አድሮ 144,000 ሕፃናትን አስፈጅቷል። ሕፃኑ ክርስቶስን ከእናቱ ጋር እንዲሰደዱ አድርጓል። ጌታችንን በገዳመ ቆሮንቶስ ፈትኗል። ትንሣኤውን በአይሁድ አድሮ አስክዷል። ሐዋርያትን አሳድዷል። አስገድሏል። ሰማዕታትን በአላውያን ነገሥታት አድሮ አስጨፍጭፏል። ቤተ ክርስቲያንን አሳድዷል። አሁን እያሳደዳት ይገኛል። ብዙዎችን በፈተናውና በመከራው ጽናትና ብዛት ተስፋ አስቆርጧል።

ሰይጣን ፈተናውን የሚያመጣው አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሰይጣንነቱን ገልጦ ጨለማ ፊቱን አሳይቶ ሳይሆን እጅግ በተለያዩና በረቀቁ ስልቶች ነው። በክፋት ብቻ ሳይሆን በፍቅር እየተመሰለ: ሃይማኖተኛና ለእምነት ተቆርቋሪ እያስመሰለ: በድካማችን ረዳት በረሃባችን ምግብ በብቸኝነታችን ወዳጅ በጭንቀታችን አረጋጊ በድህነታችን ብልጥግና ሆኖና መስሎ ነው የሚቀርበን። ይኽንንም ወደ ጌታችን ቀርቦ መራቡንም አይቶ “ይኽን ድንጋይ ዳቦ አድርገህ ብላ” ካለው መረዳት ይቻላል። (ማቴ.፬፥፬)

በክርስትና ስንኖር ወደድንም ጠላንም ፈተና ከሦስቱ መንገዶች ቢያንስ በአንዱ ወደ እኛ መምጣቱ አይቀርም። እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ክርስቲያን ኾኖ ያለ ፈተና መኖር ጨርሶ አይቻልም። ከሰው ርቀው በበረሓ ቢኖሩ: ከኃጢአት ተለይተው ቅድስናን ገንዘብ ቢያደርጉ: በዚኽ ዓለም ሀብትና ክብር ቢከበቡ: የመጨረሻውን የሥልጣን ቁንጮ ቢጨብጡ ያለ ፈተና መኖር አይቻልም።አለመቻሉንም ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው አስረድተዋል። ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ “ወዮ ለዓለም፤ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና” ብሏል። ማቴዎስ 18፥7። በሌላኛው ወንጌሉም ““በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎ አስረድቶናል።( ዮሐ.፲፮፥፴፫)

በክርስቶስ ለሐዋርያነት የተጠራና ከእርሱም የተማረው ቅዱስ ጴጥሮስ መከራና ፈተና የማይቀሩ በመኾናቸው “ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።

ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር” በማለት በስፋት የመከረን (፩ኛ ጴጥ.፬:፲፪-፲፮) ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ፈተናና መከራ አንዱ የተጠራንለት መኾኑን “በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና” በማለት አስተምሮናል (ፊል.፩:፳፥-፴ )

ይኽንን እውነታ ያልተረዱ አንዳንድ ምእመናን ክርስቲያን በመኾናቸው ብቻ በራሳቸው: በቤተሰባቸው: በቤተ ክርስቲያን: በማኅበረ ምእመናን ላይ ፈተና መከራና ስደት ሲመጣ ይረበሻሉ። እግዚአብሔርን ለምን ብለው ይሞግታሉ። እምነታቸው ስሕተት ያለበት መስሎ ይታያቸዋል። በስም ክርስቲያን የተባሉና በዙርያቸው የሚኖሩ በዓለሙ ደልቷቸው የሚኖሩ “ክርስቲያን” የሚባሉ ሰዎች ያላቸውን ሰላም: የሚያገኙት በረከትና ስኬት እያዩ ክርስትናቸውን በምድራዊ በረከት መመዘን ይጀምራሉ።  በተለይ ደግሞ በዘመናችን እያየነው እንዳለነው የፈተናው ምንጭ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች መኾናቸውን ሲያዩ እጅጉን በእምነታቸው የሚናወጹ አሉ። ይኽ ግን ክርስትናው ከዘመናችን ለመድረስ ያለፈበትን እጅግ ውጣ ውረድ የበዛበትን ጉዞ ካለመረዳት የሚመጣ ነው።የመጀመርያው የክርስትና ፈተና የመነጨው ከጌታችን እግር ተቀምጦ ይማር የአንደበቱን ቃል ይሰማ የእጁንም ተአምራት ያይ ከነበረው ከይሁዳ ነው።

ይቀጥላል !

ክርስቶስ ተከፍሎአልን ? (፩.ቆሮ.፩፥፲፪)

ዲን ታደለ ፈንታው( ዶ/ር)

                           

ክፍል  ሁለት

 

 የሰው ልጆች በክርስትና አስተምህሮ

 

የሰው ልጅ አንድ ሆኖ ተፈጥሮ ሳለ በቦታ ምክንያት አንዱ ወደ ቀኝ ሌላው ወደ ግራ ወይም ደግሞ አንዱ ወደ ሰሜን ሌላው ወደ ደቡብ ይጓዛል፡ በዚያም በሚኖርበት ስፍራ እንደ መጽሐፍ ቃል ይባዛል፤ ምድርንም ይሞላታል፡፡ ከዚህም የተነሣ በተለያየ መልክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ፣ ሥርዓት፣ እምነት  መኖሩ የተለመደ ሆነ፡፡ ይህንንም ብዝኃነት ክርስትና የሚቀበለው እንጂ የሚቃወመው አይደለም፡፡

ከመጀመሪያው አንድ ሆኖ የተፈጠረ የሰው ልጅ በቋንቋ፣ በባህል፣ በኑሮ፣ በአስተሳሰብ፣ በሥልጣኔ፣ በአኗኗር የተለያየ ቢሆንም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባሕርያችንን ነሥቶ ሰው ሲሆን፤ በመስቀሉም ጥልንና ሞትን አጥፍቶ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት አንድ አድርጎናል፡፡ የሰው ልጅ በጥንተ ተፈጥሮ አንድ ሆኖ የተፈጠረ በዘመኑ ፍጻሜም በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ሆኗል፡፡

ነገር ግን የሰው ልጅ ከውድቀት በኋላ በእርሱ ዘንድ ባለች የኃጢአት ዝንባሌ ምክንያት ልዩነትን እንደ ውበት ሳይሆን እንደ ቅራኔ መነሻ ለመለያያ እሳቤ ሲጠቀምበት ይስተዋላል፡፡ ይህም ልዩነት የመጣላት፣ የመገፋፋት ምንጭ በመሆን እያደገ እና እየሰፋ መጥቶ በወንድማማቾች መካከል እንኳን እስከ መገዳድል የሚያደርስ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ከሃይማኖታዊ (ከኦርቶዶክሰዊ) አስተምህሯችን ጋር ፈጽሞ የሚቃረን ነው፡፡ ስለሆነም “ክፉውን ከመካከላችሁ አስወግዱት” ተብሎ እንደተፃፈ በክርስትና ሕይወታችን ውስጥ ቆርጠን ልንጥለው ይገባል፡፡

ስለ ሰው ልጆች ክብር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ምን ይላል?

የሰው ልጅ ባሕርይ አንድ ከሆነ ክብሩም በሁሉም የሰው ልጀች ዘንድ አንድ እንጂ ሌላ አይሆንም፡፡ እኩልነት እና ወንድማማችነት የዚሁ ተመሳሳይ ባሕርይ ክብር እንጂ ችሮታ ወይም ግኝት ወይም የፖለቲከኞች ይሁንታ አይደለም፡፡

አስቀድመን ያነሣናቸው እሳቤዎች በስቶክ ፍልስፍና እሳቤ ውስጥ ሳይቀር የሚነሣ ቢሆንም እውነተኛ ቅርጽ እና ትርጉም፣ መሠረት፣ ፍኖት ጥንካሬን የሰጠው ግን ክርስትና ነው፡፡ በርግጥ ሐዋርያው እንዳለው የሰው ልጆች የሚበላለጡ ከሆነ የሚበላላጡት እግዚአብሔር በሚሰጣቸው ጸጋ ነው፡፡ ምክንያቱም የጸጋ ልዩ ልዩ ነው፡፡ “እግዚአብሔርም በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን” እንዲል፡፡ መንፈስ ግን አንድ ነው፡፡ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው፡፡ ጌታም አንድ ነው፡፡ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፡፡ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው፡፡… አካልም አንድ እንደሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፡፡ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎች ብንሆን ባሪያዎች ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን  እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ፣ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና ሁላችን አንዱን መንፈስ ጠጥተናል፡፡(፩ኛ ቆሮ.፥፲፩፥፲፯-፴፪)

የሰው ልጆች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስመ ክርስትና ሀብተ ወልድና ያላቸው ክርስቲያኖች አንድ አባት አብ፣ አንድ ጌታ መድኅን ክርስቶስ፣ አንድ ሕያው መንፈስ መንፈስ ቅዱስ፤ አንድ ተስፋ እርሱም ዘላለማዊ ሕይወት አላቸው፡፡ ይህ ሰው በመሆን ተከፍሎ የለበትም፡፡ አንድ የመኖሪያ ስፍራ እርሱም አምልኮአቸውን የሚፈጽሙባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አለቻቸው፡፡

ይቀጥላል

 

 

ክርስቶስ ተከፍሎአልን? (፩.ቆሮ.፩፥፲፪)

ዲ\ን ታደለ ፈንታው( ዶ/ር)

ክፍል አንድ

የምንኖርበት ዓለም በቅራኔዎች እና በግጭቶች የተሞላ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ግማሽ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ በግጭት ቀጠና ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ አሁን አሁን ይህ ግጭት አድማሱን አስፍቶ በአንድ ወቅት የተረጋጉ የሚባሉ የምዕራብ አውሮፓ ሀገሮች ሳይቀሩ የግጭት ሰለባ እየሆኑ መጥተዋል፡፡

ግጭቶች የሚነሡበት በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ለአብነት ያህል የ፳ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ብቻ አንስተን ብንመለከት በአንድ ሀገር ግጭት ከሚነሣባቸው እና ውጤቱም አውዳሚ ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ በዘር ምክንያት የሚከሠተው ችግር ነው፡፡ ለመሆኑ ዘር ምንድነው? የሰው ልጆች ስለ ምን በዘር ምክንያት ይጣላሉ? ስለ ምንስ የከፋ ግጭት ሰለባ ይሆናሉ? በክርስትና አስተምህሮ አንጻር እንዴት ይታያል? የሚለውን መሠረታዊ እሳቤን መመልከት ይጠይቃል፡፡

ማኅበራዊ ቅራኔን እና ግጭትን በተመለከተ ትኩረትን የሚሹ ሁለት እውነታዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች በሚነሡ ግጭቶች ግማሹ የሞት ሰለባ የሚሆነው ሕዝብ ቁጥር የሚሸፍነው መንሥኤው በዘር ምክንያት የሚነሣ ነው፡፡ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት ምክንያቱ አዶልፍ ሂትለር የእኔ ዘር ከሰው ዘር በላይ ነው፡፡ የጀርመን ዘር ከፀሐይ በታች ምርጥ ዘር ነው የሚለው ልፈፋውና እብደቱ የወለደው ውድመት ነው፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ፳፪ በሚሆኑ ሀገሮች ውስጥ የተከሠቱ ግጭቶች ነበሩ፡፡ በእነዚህ ግጭቶች የሞተው ሰው ልጅች ቁጥር ከ፫-፰ ሚሊዮን እንደሚደርስ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ የድል ነጋሪት የተጎሰመባቸው፣ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ያሰለፉ ጥፋቶች ደግሞ ከዚህ ላቅ ያለውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ በሀገሮች መካከል በተደረገ ዘርን መሠረት ያደረገ ጦርነት ወደ ፳፭ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በቀጥታ የሞት ሰለባ ሆኗል፡፡

ዘር ምንድነው?

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ዘርን፣ ዘርዕ በቁሙ፡- ዘር ቅንጣት ፍሬ የሚበቅል ማለት ነው፡፡ የሰውን ዘር ልጅ፣ ወገን ነገድ ትውልድ በማለት ይፈቱታል፡፡ በዘመናዊው ዓለም ዘር የሚለው ቃል ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም በአውሮፓውያን የቋንቋ ጥናት መጀመሪያ የተከሠተው በ፲፮ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በ፲፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ተመራማሪዎች ዘርን፣ እንዲሁም ቤተሰብን ለመግለጥ ተጠቅመውበታል፡፡ ጀርመኖች ቃሉን በ፲፰ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የቆዳ ቀለማቸው እና አካላዊ ቅርጻቸው የተለያዩ ወገኖችን (የሰው ልጆችን) ለመግለጽ ተጠቅመውበታል፡፡ ሌላ ተመራማሪ ዘርን ነጭ፣ ቢጫ፣ ጥቁር፣ እና ቀይ በማለት የቆዳ ቀለምን ለመለየት ተጠቅሞበታል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ ቋንቋ ያለ ቦታው ገብቶ ዘርን ለመግለጥ ጥቅም ላይ ውሎ የመለያየት እና የመበታተን አደጋ ሲሆን እንመለከታለን፡፡

ዘረኝነት ምንድነው?

ዘረኝነት የሰው ልጆችን የሚነጣጥል፤ ደረጃ የሚሰጥ እና እኛ እና እነርሱ በሚል ጎራ የሚከፋፍል ነው፡፡ ይህንንም ሁኔታ ተከትሎ የሰው ልጆችን ወደማያባራ ውስብስብ ጥላቻ ውስጥ የሚከት የማኅበረሰብ ስብራት ነው፡፡ ዘረኝነት የሰው ልጆችን ከዚህ የክፍፍል አጥር ውጭ አድርጎ አይመለከታቸውም፡፡

ሰዎችን ወደ አንድነት ወይም ወደ ልዩነት የሚመራ አውዳሚ እሳት ነው፡፡ በዘረኝነት የታወሩ ሰዎች ደግሞ ሲመሩት ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ይህ አመለካከት ከክርስትና አስምህሮ ምሰሶዎች ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ እርሱም የሰው ልጆችን አንድነት “ሁሉም የአንድ አዳም እና አንድ የሔዋን ልጆች እንጂ ሌላ አይደሉም” ከሚለው አስተምህሮ፣ ከሰው ልጅ ክቡር ባሕርይ እና ከክርስቲያናዊ መንፈሳዊነት እሳቤ አንጻር ዘረኝነት ስፍራ የለውም፡፡ ሰው ሠራሽ እና ጨካኞች የወለዱት ከፋፋይ እና አውዳሚ አስተሳሰብ ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘረኝነትን የምትቃወምበት መጽሐፍ ቅዱሳዊና ትውፊታዊ አስተምህሮ መነሻ አላት፡፡

ስለ ሰው ልጆች አንድነት ክርስትና የሚያስተምረው

አስቀድሞ በአይሁድ እምነት ዘንድ የነበረው የተስፋ ቃልም ይሁን ወንጌል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው የሰው ልጆችን ፍጹም አንድነት የሚቀበል ነው፡፡ ይህም ትምህርት እግዚአብሔር አንድ ነው ከሚለው ይጀምራል፡፡ እግዚአብሔር የመጀመሪያም የመጨረሻም (አልፋ እና ኦሜጋ) እርሱ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ድኅነት አንድነት እና ዓለም አቀፋዊነት መነሻ ሲናገር መነሻው ቅድስት ሥላሴን ማእከል ያደረገ ነው፡፡ የእነርሱን የማትከፈል አንድነት ለሰው ልጆች አንድነት መሠረት አድርጎ ተናግሯል፡፡

የዘረኝነት ድምዳሜ የሚያመራው ደግሞ በተግባር እግዚአብሔርንና መንግሥቱን በመካድ ነው፡፡ የእስራኤል ነቢያት ራሳቸውን በዘር ብቻ ሳይሆን በተለያየ የየራሳቸው አማልክት ከፋፍለው ምድርን ዕረፍት ነሥተው የነበሩት በተሳሳተ ዕሳቤ ላይ በመቆማቸው ነበር፡፡ እውነተኞቹ ነቢያት የቀደሙ ሰዎችን ሲገሥፁ የተናገሩት “እግዚአብሔር የሁሉም በሁሉም ያለ፤ ሁሉን ቻይ ጌታ ነው” የሚል አስተምህሮን ወደ ዓለም በማምጣት ነው፡፡ አበው ኦሪት ዘፍጥረትን መነሻ አድርገው የሰው ልጆችን አንድነት አምልተው አስፍተው አስተምረዋል፡፡

ሔዋን ከአዳም ግራ ጎን ተገኘች፤ ሕያዋን የሆኑ የሰው ልጆችንም በሩካቤ አስገኘች ማለት ሌላ አይደለም የሰው ልጆች ግንድ አንድ ነው ማለት ነው፡፡ የሃይማኖት ድንጋጌዎች፣ ቀኖናዎች ሕግጋት ሁሉ የሰው ልጆችን መገኛ ግንድ አንድ አዳምን ማድረጋቸው (the absolute homogeneity of human nature) ፍጹም የሰው ልጆችን ፍጹማዊ አንድነት የሚያረጋግጥ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

ሔዋን (የሕያዋን ሁሉ እናት) ሌላ ፍጥረት ሳትሆን ከአዳም ከግራ ጎን መገኘቷ ከአንዱ አዳም ጎን የተከፈለች እንጂ ሌላ ልዩ አካል አለመሆኗን እናውቃለን፤ እናምናለንም፡፡

እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ሲል እግዚአብሔር የሰው ልጆች አንድነት እየተገለጠ ነው፡፡ እግዚአብሔር በአካል ሦስት እንደሆነ እናምናለን፡፡ ነገር ግን በባሕርይ፣ በአገዛዝ፣ በመለኮት፣ በሥልጣን፣ በእግዚአብሔርነት፣ በዘላለማዊነት፣ ዓለምን በመፍጠር አንድ አምላክ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ሰው አንድም ብዙም ነው፡፡ የአንበሳ ዘር አንድ፣ የነብር ዘርም አንድ ነው፡፡ የሰው ዘርም እንዲሁ ሰው ነው፡፡

የትም ይወለድ የትም ይደግ የሰው ልጅ ሰው ነው፡፡ መርጦ የሚያገባውም ጃፓናዊት ትሁን ኮርያዊት እስያም ትሁን አውስትራሊያ ሰው በመሆኗ ነው የባሕርይ አንድነቱን ተመልክቶ ገንዘብ የሚያደርጋት፡፡ ሰው በሚኖርበት አካባቢም በቆዳ ቀለሙ አንዱ ከአንዱ ሊለያይ ይችላል፡፡ በቋንቋ፣ በባህልም እንዲሁ ነው፡፡ ይህ ግን የሰው ዘር መሆኑን ሰውነቱን ሊቀይር የሚችል አይደለም፡፡ የሰው ልጆችም አማራ ይሁኑ ኦሮሞ አፋር ይሁኑ አርጎባ፤ ፈረንሳዊ ይሁኑ እንግሊዛዊ ሰው ተብለው ይጠራሉ እንጂ ሌላ ከሰውነት ተራ ወጥተው የሚጠሩበት መጠሪያ የላቸውም፡፡

ይቆየን

ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት (ጸሎተ ሃይማኖት )

                                                                 በመ/ር ተመስገን ዘገዬ
ጥምቀት በጽርዕ ቋንቋ “ኤጲፋኒ “ በግእዙ “አስተርእዮ ” በአማርኛው “መገለጥ ” የሚል ትርጉም የያዘ ቃል ነው ፡፡ቤተ ክርስቲያናችን ከበዓለ ልደቱ ቀጥላ ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ወጥታ በዱር በሜዳ በወንዝ በባሕር ዳርቻ ጥር ፲፩ ቀን በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት የምታከብረው በዓለ ጥምቀቱን ነው፡፡
ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት በዓላት በሦስተኛ ደረጃ የሚገኘው በዓለ ጥምቀት ነው፡፡መጋቢት ፳፱ ቀን በየዓመቱ የምናከብረው በዓለ ጽንሰቱ አንድ ተብሎ ተቆጥሮ በሁለተኛ ደረጃ ታኀሣሥ ፳፱ ቀን የምናከብረው በዓለ ልደቱ ነው፡፡በሦስተኛው ደረጃ ጥር ፲፩ ቀን በየዓመቱ የምናከብረው በዓለ ጥምቀቱ ነው፡፡
ጥምቀት አጥመቀ፤ አጠመቀ (ነከረ)፣ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣት፣መጥለቅ ማለት ነው፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውና የሌሎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር ነው፡፡ በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡ ፻፶አባቶች ‹‹ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት፣በአንዲት ጥምቀት እናምናለን፡፡)››በማለት እንደመሰከሩት፡፡መንግሥተ ሰማይ ለመግባት መጠመቅ ግድ ነው፡፡
ጥምቀት ምሥጢር የተባለበት ምክንያት፡- ላመኑ እንጂ ላላመኑ አይሰጥም፣
በዐይን የሚታየው በእጅ የሚዳሰሰው ውኃ በግብረ በመንፈስ ቅዱስ ማየ ገቦ ሲሆን አይታይምናምእመናንም ጥምቀት በሚታየው የማይታየውን ጸጋ ሲቀበሉ አይታይም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኅቱም ድንግልና ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና ተወለደ (ትምህርተ ሃይማኖት ርትዕት_ በማኀበረ ቅዱሳን )
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በስምንት ቀን ቤተ ግዝረት በ፵ ቀኑ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ዕጒለ ርግብ ዘውገ ማዕነቅ ይዞ በመግባት ሕግ መጽሐፋዊን ሕግ ጠባዕያዊን ሲፈጽም ለእናቱ እየታዘዘ አድጎ ፴ ዓመት ሲሆነው ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሔደ በተወለደ በ፴ ዘመኑ በዘመነ ሉቃስ ጥር ፲፩ ቀን ማክሰኞ ከሌሊቱ ዐሥር ሰዓት በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ (አምስቱ አዕማደ ምሥጢር ወምስለ ሥነ ፍጥረት )
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፴ ዘመኑ በባሕረ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ አብነት ሰው ሁሉ ይድን ዘንድ መጠመቅ እንዳለበት ተናገረ‹‹ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል›› (ማር.፲፮፥፲፮)
ጌታችን ለጥምቀት ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በወረደ ጊዜ ቅዱስ ዮሐንስም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ጌታዬ እኔ በአንተ ልጠመቅ ይገባል እንጂ አንተ በእኔ ትጠመቃለህን? ገለባ ከእሳት ፊት ይቆማልን? እኔስ ከአንተ ፊት እንደምን እቆማለሁ? በማለት ተከራክሮ ነበር፡፡(ማቴ.፫፡፲፬) ጌታም ‹‹ወይደልወነ ከመ ንፈጽም ኵሎ ሕግ፤ሕግን ሁሉ ልንፈጽም ይገባናል›› አለው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ በዮርዳኖስ በኢየሩሳሌም በይሁዳ አውራጃዎች ከጌታ ቀድሞ ‹‹መንግሥተ ሰማያት በልጅነት በእምነት በጥምቀት ልትሰጥ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ከኃጢአት ከበደል ተመለሱ ›› እያለ ለኃጢአት ሥርየት የንስሓ ጥምቀት ያጠምቅ ነበር፡፡
እስራኤላውያንም በብዛት ወደ እርሱ እየመጡ የንስሓ ጥምቀትን ይጠመቁ ነበር ፡፡(ማቴ.፫፡፭-፮ ) ብዙ ሰዎችም ከኃጢአታቸው እየተናዘዙ በዮሐንስ ይጠመቁ ነበር ቢሆን ፍጹም ሥርየተ ኃጢአትን ልጅነትና ድኅነተ ነፍስን አያገኙም ነበር፡፡
ጌታችን ለመጠመቅ ወደ ባሕረ ዮርዳኖስ በወረደ ጊዜ ምድር ተጨነቀች የዮርዳኖስ ውኃም ግማሹ ወደ ቀኝ ግማሱ ወደ ግራ ሸሸ፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም የጌታችንን ጥምቀት በትንቢት መነጽርነት አስቀድሞ በማየት ‹‹ ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ አድባር አንፈርዐጹ ከመ ሐራጊት ወአውግርኒ ከመ መሓስአ አባግዕ ምንተ ኮንኪ ባሕር ዘጎየይኪ ወአንተኒ ዮርዳኖስ ዘገባእከ፤ድኅሬከ ፡ባሕር አየች ሸሸች ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ ተራሮች እንደ ኮርማዎች ኮረብታዎችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፡፡ አንቺ ባሕር የሸሸሽ አንተ፣ ዮርዳኖስ ወደ ኋላ የተመለስክ ምን ሆናችኋል? እናንተ ኮረብቶችስ እንደ ጠቦቶች ለምን ዘለላችሁ››ይላል (መዝ.፻፲፫(፻፲፬)፥፫-፮)
ቅዱስ ቄርሎስም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ ውኃዎች እንደ ሞቀ ውኃ ፈሉ ይላል፡፡ ይህ አስደናቂ ሥራ በአንድ በኩል የክርስቶስ መለኮታዊ ኃይል ሲያመለክት በሌላ በኩል ደግሞ ማንም ሰው በክርስቶስ አምኖ መንፈስ ቅዱስን እንደሚገኝ ያሳያል፡፡
ጌታችን ተጠምቆ ከውኃ ሲወጣ አብ በደመና ሁኖ ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ሎቱ ስምዕዎ፤የምወደው ልጄ ይህ ነው እሱን ስሙት››ብሎ የባሕርይ ልጅነቱን መስክሮለታል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ፀዓዳ ወርዶ በራሱ ላይ ዐርፎበታል፡፡ መንፈስ ቅዱስ መሆኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ? ጌታችን የተጠመቀው በዐሥረኛው ሰዓት ሌሊት ነው በዚህ ሰዓት ደግሞ ተዋሐስያን ቦታቸውን ለቀው አይንቀሳቀሱም (አምስቱ አዕማደ ምሥጢር ወምስለ ሥነ ፍጥረት )
ጌታችን በማየ ዮርዳኖስ በፍጡሩ እጅ በዕደ ዮሐንስ መጠመቁ ኃጢአት ኖሮበት ሥርየት ለመቀበል አይደለም፡፡ለጌታችን መጠመቅ ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ መውረድን በግልጥ ለማሳየት ሲባል ታቦታተ ሕጉ በካህናት ተይዘው ወደ ሜዳና ወንዝ ዳር በመሄድ ኢትዮጵያውያን በቅዳሴ በውዳሴ፣ በዝማሬ በዕልልታ፤በከበሮ ፤በጽናጽል በክብር በዓለ ጥምቀቱን በታላቅ ድምቀት ያከብሩታል ፡፡
ጌታችንም የተጠመቀበት የጥር ወር በዕብራውያን (እስራኤል) አገር የዝናብና የበረዶ ወራት ስለሆነ እንኳንስን ከወንዝ ዳር ከማንኛውም ቦታ ቢሆን ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም ነበር፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም (315-386 ዓ/ም) ‹‹ወደ ውኃ በወረድን ጊዜ ውኃነቱን ሳይሆን በውኃው አማካኝነት የምናገኘውን ድኅነት ተመልከት››ይላል፡፡
ጥምቀት በኦሪት ጊዜም ነበር ፡፡ ኢዮብና ንዕማን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀው ከደዌ (ከሕመም) ድነዋል፡፡ ኢዮብና ንዕማን የአዳምና የልጆቹ ምሳሌ፤ደዌው (ሕመሙ) የመርገመ ሥጋ ወነፍስ ምሳሌ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ ነው (፩ኛ ነገስ ፭፡፰-፲)
ነብዩ ኤልሳዕ የደቀ መዝሙሩን መጥረቢያ ባሕረ ዮርዳኖስ ወንዝ ገብቶበት በነበረ ጊዜ የእንጨት ቅርፊትን አመሳቅሎ ውኃው ላይ ቢጥለው መዝቀጥ( መግባት) የማይችለው ቅርፊት ዘቅጦ( ገብቶ) መዝቀጥ የማይገባውን ብረት ይዞት ወጥቷል፡፡ ይህም ምሳሌ ነው የእንጨቱ ቅርፊት የጌታ ብረት የአዳም ዮርዳኖስ ወንዝ የጥምቀት (የሞት የመቃብር) ምሳሌ ሲሆን መዝቀጥ ( መግባት) የማይገባው ቅርፊት ዘቅጦ መዝቀጥ የሚይገባውን ብረት ይዞ መውጣቱ መሞት የማይገባው አምላክ ሞቶ ሞት የሚገባውን አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው፡(፪ኛ.ነገ.፮፡፩-፯)
ጌታችን ለምን በ፴ ዘመኑ ተጠመቀ?
ሰው ሁሉ በ፴ ዘመኑ ሕገ ነፍስን ይሠራልና ለአብነት አንደም ቅስና ምንኩስና በ፴ ዘመን ይገባል ሲል ነው፡፡ ቀጥሎም አዳምን የ፴ ዘመን ጎልማሳ አድርጎ ፈጥሮት የሰጠውን ልጅነት አስወስዶ ነበርና የአዳምን ልጅነት ለመመለስ በ፴ ዘመኑ ተጠመቀ
                                ጌታችን ለምን በባሕረ ዮርዳኖስ ተጠመቀ?
፩. ትንቢቱና ምሳሌውን ለመፈጸም ፦ጌታችን አምላካቸን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ እንደሚጠመቅ ከልደተ ክርስቶስ በፊት በአንድ ሺህ ዓመተ ዓለም ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት የዘመራቸው የትንቢት መዝሙሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ትንቢቱ፡ “ቃለ እግዚአብሔር ላዕለ ማያት አምላከ ስብሐት አንጎድጎደ እግዚአብሔር ላዕለ ማያት ብዙኀ ፤የእግዚአብሔር ቃል በውኃዎች ላይ ነው፡የተመሰገነ አምላክ ድምጹን አሰማ እግዚአብሔር በብዙ ውኃዎች ላይ ነው፡፡”(መዝ.፳፰፥፬)
“ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርሁ ደንገጹ ቀላያተ ማያት ወድምጸ ማያቲሆሙ ፤አቤቱ ውኃዎች አዩህ ውኃዎች አዩህና ፈሩህ፤የውኃዎች ጥልቆች ደነገጡ ማዕበላቸውም ተሰማ”(መዝ.፯፥፮)“ በእንተዝ እዜከረከ እግዚኦ በምድረ ዮርዳኖስ በአርሞንኤም በደብር ንዑስ ቀላይ ለቀላ ትጼውኦ በቃለ አስራቢከ፤ሥለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ኮረብታ አስብሃለሁ ………(መዝ.፵፩፥፮)
‹‹ ባሕርኒ ርእየት ወጎየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኀሬሁ አድባር አንፈርዐጹ ከመ ሐረጊት ፤ባሕርአየች ሸሸችም ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ ተራሮች እንደ ኮርማዎች ኮረብታዎችም እንደ ጠቦቶች ዘለሉ፡፡ አንቺ ባሕር የሸሸሽ ዮርዳኖስም ወደ ኋላሽ የተመለሽ ምን ሆናችኋል? ›› በማለት ነብዩ አስፍቶና አጉልቶ ዘምሮአል፡፡ ይህ ትንቢት ስለነበር ጌታችን ከሌሎች አፍላጋት ሁሉ መርጦ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ (መዝ.፻፲፫፡፥፫-፭)
ምሳሌው፡- አባታችን አብርሃም ነገሥተ ኮሎዶ ጎሞርን ድል አድርጎ ከገንዘቡ ዐሥራት በኲራት በማውጣት ዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ካህኑ መልከጼዴቅ ሲሄድ ኅብስተ አኮቴት ጽዋዐ በረከት ይዞ ተቀብሎታል፡፡አብርሃም የምእመናን የዮርዳኖስ ወንዝ የጥምቀት ካህኑ መልከጼዴቅ የቀሳውስት፤ኅብስተ አኮቴት ጽዋዐ በረከት የሥጋ ወደሙ ምሳሌ ነው(ዘፍ.፲፬፥፲፯፣ዕብ ፯፡፩-፰)
ዮርዳኖስ አንድ ወንዝ ሲሆን ዝቅ ብሎ በዮር እና በዳኖስ ተለይተዋል፡፡ዮር በእስራኤል በኩል ያለው ሲሆን ዳኖስ በአሕዛብ በኩል ያለው ነው፡፡ዝቅ ብሎ ደግሞ ሁለቱም ተገናኝተዋል፡፡ ሁለቱ በተገናኙበት ቦታ ጌታ ተጠምቋል፡፡ ይህ ምሳሌ ነው፡፡
ዮርዳኖስ ከላይ አንድ እንደሆነ ሁሉም የሰው ዘር የአንድ የአዳም ልጅ እንደሆነ ሲያስረዳ ዝቅ ብሎ መለየቱም እስራኤል በኦሪት አሕዛብ በጣዖት ተለያይተዋል፡፡ ዝቅ ብሎ መገናኘቱ ሁሉም በአንድ ወንጌል የማመናቸው ምሳሌ ነው፡፡
ጌታችንም ሁለቱ ከተገናኙበት ቦታ ተጠመቀ ሁላችሁንም አንድ ላደርጋችሁ መጥቻለሁ ሲል ነው፡፡ ሌላው ምሥጢር ግን አዳምና ሔዋን ሕግ ተላልፈው ከገነት ተባረው ጸጋቸው ተገፎ ራቁታቸውን ሆነው ከገነት ሲወጡ ዲያብሎስ የጨለማ ግርዶሽ ጋርዶ ፍዳ አጽንቶባቸው አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፤አዳም የዲያብሎስ ወንድ አገልጋይ ነው፤ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ፤ ሔዋን ደግሞ የዲያብሎስ ሴት አገልጋይ ናት፡፡ ብላችሁ ስመ ግብርናትን ጽፋችሁ ስጡኝ አላቸው፡፡ እነርሱም ፍዳ የሚያቀልላቸው መስሏቸው እንዳላቸው አድርገው አዘጋጅተው ሰጡት ዲያብሎስም ያንን የዕዳ ደብዳቤ አንዱን በሲዖል አንዱን በዮርዳኖስ ወንዝ አኖረው፡፡
ዲያብሎስ በዮርዳኖስ ወንዝ ያስቀመጠውን የዕዳ ደብዳቤ ጌታ በጥምቀቱ ጊዜ እንደ ሰውነቱ ረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶታል፡፡ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በሰኞ ውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ‹‹ወሰጠጠ መጽሐፈ ዕዳሆሙ ለአዳም ወለሔዋን ፤የአዳምንና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደላቸው›› ይላል፡፡(ቆላ.፪፡፲፫)፡፡በአዳምና በሔዋን አንጻር የእኛንም የዕዳ ድበዳቤያችን ቀደደልን ፡፡
ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሄዶ የተጠመቀበት ምክንያት
ትሕትናን ሲያስተምር ነው፡፡ምነው ጌታ ፈጣሪ፤ እግዚእ ሲሆን ወደ ትሑት ዮሐንስ ሄደ ቢሉ ሥጋ መልበሱ ለትሕትና ነውና፡፡ይህ ባይሆን ዛሬ ነገሥታት ቀሳውስትን ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን አቁርቡን ይሉ ነበርና፡፡
ትንቢቱና ምሳሌውን ለመፈጸም (ት.ሕዝ ፴፮፡ መዝ.፻፲፫፡፥፫-፭)
ጌታችን መድኃኒታችን መጠመቅ ለምን አስፈለገው?
1.ጥምቀት ለሚያስፈልገን ለእኛ አርአያ ለመሆን ፡-እርሱ ተጠምቆ ተጠመቁ ባይለን ኑሮ ጥምቀት አያስፈልግም፡፡ አስፈላጊ ቢሆንማ ጌታ ራሱ ተጠምቆ አብነት በሆነን ነበር እንዳይሉ መናፍቃን ምክንያት አሳጣቸው፡፡
ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስም” ወአርኃወ ለነ አንቀጸ ጥምቀት ከመ ንጠመቅ፤ እንጠመቅ ዘንድ የጥምቀትን በር ከፈተልን”ሲል የጥምቀትን ምስጢር ያስረዳናል፡፡
2. ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ፡- ‹‹አቤቱ ውኃዎች አዩህ ውኃዎች አይተውህ ፈሩ ጥልቆችም ተነዋወጡ ወኃዎችም ጮሁ ደመኖችም ድምጽን ሰጡ ፍላጾችም ውጡ ›› (መዝ.፸፯፡፲፮-፲፯) የሚል ትንቢት ነበርና ይህ እንዲፈጸም፡፡
3. በዮርዳኖስ ውስጥ የነበረውን የዕዳ ደብዳቤ ለመደምሰስ፦ ( ሰኞ ውዳሴ ማርያም)
አንድነትና ሦስትነቱን ለማስረዳት፡- ከዚህ በፊት የሥላሴ አንድነት ሦስትነት በግልጽ አይታወቅም ነበር፡፡ ጌታ በዮርዳኖስ በሚጠመቅበት ጊዜ ግን ምሥጢረ ሥላሴ ግልጽ ሁኖ አብ በደመና ሁኖ የምወደው ልጄ ይህ ነው በማለቱ የወልድ አባት መሆኑ ታወቀ፡፡ መንፈስ ቅዱስም የባሕርይ ሕይወቱ መሆኑ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጦ ሲታይ ወልድ በተለየ አካሉ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ታየ ተገለጠ፡፡
ጌታን ተጠምቆ ከውኃ ሲወጣ የሚከተሉት ተአምራት ተፈጽመዋል
1.ሰማያት ተከፈቱ፡- ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ከውኃው ሲወጣ “ወናሁ ተርኀወ ሰማይ ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ ከመ ርግብ ወነበረ ላዕሌሁ፤ሰማይ ተከፍቶ መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት አየ ” አሁን ሰማይ የሚዘጋና የሚከፈት ሁኖ ሳይሆን ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ ምሥጢር ተገለጠ፡፡ማለትም የልዑል እግዚአብሔርአንድነት ሦስትነቱ ምሥጢር ጎልቶ ወጣ ለማለት ነው፡፡
2. መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ
እግዚአብሔር አብ ከላይ ‹‹ መጽአ ቃል እምደመና ዘይብል ዝንቱ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ወሎቱ ስምእዎ፤ ለተዋሕዶ የመረጥሁት በእርሱ ሕልውና በመሆን ልመለክበት የወደደሁት ልጄ ይህ ነው›› (ማቴ.፫፡፲፯) በማለት የባሕርይ አምላክነቱን መስክሯል፡፡ወንጌላውያኑ በዚህ ቃል ምሥጢረ ሥላሴን በግልጽ አስተምረውናል፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለምን በውኃ ተጠመቀ?
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ ተጠምቋል ጥምቀቱ በውኃ የሆነበት ምክንያት ‹‹ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ ›› ይላል (ማቴ፫፡፲፮) በቃሉም እንዲህ አስተማረ ‹‹ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ መንግስተ ሰማያ ይገባ ዘንድ አይቻልም›› (ዮሐ.፫፡፭) በቅዱሳን ነቢያትም ሲነገር የነበረ ትንቢት ነበር‹‹ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ ከርኩስታችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ፡፡( ት.ሕዝ. ፴፮፥፳፭) የሚል አስቀድሞ ትንቢት ተነግሮ ነበር፡፡
ውኃ የሰውነትን ቆሻሻ እንደሚያጠራ ጥምቀትም የነፍስን ኃጢአት ያጠራልና፡፡አንድም ውኃ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይፈሳል ጥምቀትም ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይከናወናልና፡፡ አንድም ውኃ በዙፋኑ ካለ ንጉሥ አንስቶ በዐደባባይ እስከ አለ ችግረኛ ሁሉ የተሰጠ በሁሉ ቤት የሚገኝ ነው፡፡
ጥምቀትም የተሠራው ለሰው ሁሉ ነው፡፡ ጎሳ፣ጎጥ፣ቀለም፣ደሀ፣ሀብታም አይለይበትም፡፡ አንድም በውኃ የታጠበ ልብስ ጥንካሬ እንደሚያገኝ ምእመናንም በውኃ ተጠምቀው ገድልና ትሩፋት እየሠሩ በጥምቀት ባገኙት ኃይል ባላጋራቸውን ዲያብሎስን ድል ይነሱታል፡፡ አንድም የርብቃ ለይስሐቅ መታጨት በውኃ ምክንያ ሁኗል (ዘፍ.፳፬፡፲-፳፯) መንፈሳዊ መታጨትም (ለእግዚአብሔር መንግሥት) በውኃ (በጥምቀት) ሁኗል፡፡
ጌታችን በማር በወተት ጥምቀቱን ማድረግ ሲቻለው በውኃ ያደረገበት ምክንያት ማርና ወተት በሁሉ አይገኝምና ሁሉም በሚያገኘው አደረገው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም ከአምላካቸው በቃልና በተግባር የተማሩትን በሥራ ሲተገብሩ ሕዝቡን በውኃ አጥምቀዋል፡፡
ለጥምቀት የውኃ አስፈላጊነት በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ-፫ ላይ ተደንግጓል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀት በዓልን የምታከበረው የጌታችን የማዳኑን ምስጢር ለማዘከርና ለመመስከርም ነው፡፡አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ “የጠበሉን መረጨት አይተው በቀድሞ ዘመን ወደ ሀገራችን መጥተው የነበሩ መናፍቃን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ይህን ምትፈጽመው ጌታችን ለእኛ ብሎ ያሳየውን ትሕትና ለመመሥከር ለምእመናን የጌታችን በረከተ ጥምቀት ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ምእመናን እየመለሰች በየዓመቱ አታጠመቅም” ብለዋል፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀትን የምታከብረው፣የበዓሉን ጥንታዊነት በጠበቀ መልኩ በመሆኑ ሀገራችንን በዓላም እንድትታወቅ የበርከታ ጎብኚዎች መስህብ እንድትሆን አድርጓታል ።” የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነስታችሁ ተከተሉት” (ኢያ.፫፥፫)
በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው።የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ መጓዝና ወደ ወንዝ መውረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልዓዛር ጊዜ ነው።
ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም(ይከተር ) ነበር።እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስ ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቁራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው።
ኢያሱ የጌታ ምሳሌ፣እስራኤል የምእመናን ፣ዮርዳኖስ የጥምቀት ፣ምድረ ርስት የገነት የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው።
ታቦቱን አክብሮ የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ ፣ታቦቱ የጌታችን፣ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ: ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሓ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ነው፡፡

                የደወሉ ምሥጢር

 

መ/ር ለይኩን አዳሙ(ባሕር ዳር)

  ደወል ማለት ምን ማለት ነው ? ቢሉ ‹‹ጠቅዐ›› መታ፣ደወለ አቃ ጨለ፣አነቃቃ፣አነሳሳ፣ አሳሰበ ከሚለው የግእዝ ግስ የተወሰደ ሲኾን ትርጉሙም መጥቅዕ፣ መረዋ፣ቃጭል ማለት ነው፡(ኆኅተ ሰማይ በቀሲስ ያሬድ ገ/መድኀን)

ደወል ከብር፣ከነሐስ፣ከብረት እና ከመሳሰሉ ድምፅ ሰጪ ከኾኑ ነገሮች በመጠኑ አነስተኛ፣መካከለኛ፣በጣም ግዙፍ ኾኖ ይዘጋጅና ከፍ ካለ ቦታ ላይ ወይም ዛፍ ላይ ይንጠለጠልና ከውስጥ የምትገኘውን ምላስ የምትመስል ብረት በረጅም ገመድ በማሰር ከታች ገመዱን በማወዛወዝ ደወሉን በመምታት ድምጽ እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

ደወል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለመንፈሳዊ አገልግሎት ከሚውሉት ንዋያት ቅዱሳት አንዱ ሲኾን በቤተ ክርስቲያን  በተለያዩ ጊዜያት ይደወላል፡፡ ሲደወልም ራሱን የቻለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሥጢርና ትርጉም አለው፡፡ይህንም በቅደም ተከተል የምናየው ይኾናል፡፡

ደወል መቼ ? እንዴት  ይደወላል?

  በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አምስት ጊዜ ደወል ይደወላል፡፡ እርሱ ራሱን የቻለ የረቀቀና የመጠቀ ትርጉም አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የምትገለገልባቸው የከበሩ ንዋያት ምሳሌያዊና  ምሥጢራዊ ትርጉማቸውን ለመግለጽ ብቁ ናቸው፡፡

ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በትርጓሜ ወፍጮ ፈጭተው በምሥጢር መዶሻ ሰልቀውና  አለስልሰው ምሥጢረ ደወልን ሲያመሠጥሩትና ለምእመናን ዘወትር ሲመግቡት ኑረዋል ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ ለመኾኑ ደወል መቼና እንዴት ይደወላል? ብሎ የሚጠይቀን ቢኖር መልሳችን  እንደሚከተለው ነው፡፡

                       ፩ የተጋብኦ ደወል

ይህ የተጋብኦ ደወል ለአገልግሎት የተመደቡ ካህናት ወደ ቤተክርስቲያን እንዲሰበሰቡ በዋይዜማ፣ በመንፈቀ ሌሊት፣ ለሰዓታት፣ ለማሕሌት፣ ለኪዳን፣ ለቅዳሴ የቤተ ክርስቲያን በር ከመከፈቱ በፊት ይደወላል፡፡ የተጋብኦ ደወል ዓላማው የራቁትን ማቅረብ የተበተኑትን  መሰብሰብ  የተኙትን ከእንቅልፍ መቀስቀስ፣ ማንቃት ነው፡፡

የተጋብኦ ደወል የሚደወለው የዋይዜማ ሲኾን ዐሥራ አምስት ጊዜ፣ለማሕሌትና ለሰዓታት ሲሆን  ዐሥራ ሁለት ጊዜ ይደወላል፡፡ ይኽ ሁሉ ምሳሌ ነው፡፡

ዋይዜማ የኦሪት ምሳሌ ሲኾን፣ዐሥራ አምስት ጊዜ መደወሉ የዐሥራ አምስቱ ነቢያት ምሳሌ፣ድምጹ የድምፀ ነቢያት ምሳሌ ነው፡፡ የደወሉ ድምጽ ከሩቅ እንደሚሰማ ሁሉ የነቢያትም ትምህርታቸው በአራቱ ማዕዝናተ ዓለም ተሰምቷል፡፡

የነቢያትን ትምህርት ሰምተው እስራኤል ዘሥጋ ከአምልኮተ ጣኦት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰው ለጌታችን ልደት ለሐዲስ ኪዳን  እንደ ተዘጋጁ ሁሉ ዛሬም እስራኤል ዘነፍስ የደወሉን ድምፅ ሰምተው ለሰዓታት፣ለማኅሌት ፣ለጸሎት፣ለንስሓ ፣ለቊርባን ለጾም ለጸሎት ይዘጋጃሉ፡፡

መንፈቀ ሌሊት የዕለተ ምጽአት፤ እንቅልፍ የሞት ምሳሌ፤ ሊቀ ዲያቆኑ የሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ምሳሌ፤ ሊቀ ዲያቆኑ ደወሉን ደውሎ ካህናትን ከእንቅፍ ማስነሣቱ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ንፍሐተ ቀርን መትቶ ሙታንን የማንቃቱ ምሳሌ ነው (፩ኛተሰ.፬፥፲፭ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፶፪)

ካህናት ምእመናን የሙታን፣ ሙታን በንፍሐተ ቀርን ተነሥተው ጻድቃን በቀኝ ኃጥአን በግራ ቁመው ፍርድ እንዲቀበሉ ካህናትና ምእመናንም በደወሉ ከእንቅልፋቸው ነቅተው በግራ በቀኝ ቁመው እግዚአብሔርን የማመስገናቸው ምሳሌ፡፡

ዛሬ የደወሉን ድምጽ ሰምቶ ከኃጢአት ከእንቅልፍ ነቅቶ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ያላመሰገነ በኋለኛው ዘመንም ገነት መንግሥተ ሰማያት አይገባም፡፡ዛሬ ቤተክርስቲያን መግባታችን ነገ ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታችን ዋስትና ነው፡፡

የተጋብኦ ደወል መቼ ተጀመረ ? ማን ጀመረው? ብሎ ለሚጠይቀን  ሰው መልሳችን ጻድቅና ትሑት የሆነው አባታችን ኖኅ ነው፡፡ (ዘፍ ፮ ) ኖኅ የደወለውን የደወል ድምጽ ሰምተው ነፍሳት ወደ መርከቡ ገብተው ከሰማይ ከሚወርደው ዶፍ  እንደተረፉ ሁሉ ዛሬም  በቤተ ክርስቲያን የሚደወለውን ድምጽ ሰምተው ከኃጢአት፣ ወደ ጽድቅ፣ ከጨለማ ፣ወደ ብርሃን፣ ከሥጋዊ ሐሳብ ወደ መንፈሳዊ ሐሳብ ተመልሰው አማናዊቷን መርከብ ጥግ አድርገው እግዚአብሔርን ተስፋ አድርገው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን አግኝተው ያሉ የተዋሕዶ ልጆች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

በኖኀ ዘመን ግእዛን የሌላቸው የማይጠየቁ እንስሳት የደወሉን ድምጽ ሰምተው ወደ መርከቡ ገብተው ሥጋን አፍርሶ አጥንትን ከስክሶ ከሚጥል ከሰማይ ከሚወርድ ዶፍ ከሞት ሲተርፉ አእምሮ  ያላቸው የሰው ልጆች ግን የደወሉን ድምጽ ሰምተው ችላ በማለታቸው በነፍስ በሥጋ የዘለዓለም ሞት እንደገጠማቸው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡

ዛሬም ቢሆን የተፈጠሩለትን ዓላማ ረስተው በዕለተ ዓርብ የተከፈለላቸውን ዋጋ ችላ ብለው ወደ አማናዊቷ መርከብ መምጣታቸውን ትተው ቀኝና ግራ የሚቀጥፉ እጅግ ብዙ ናቸው፡

ወዳጄ አንተስ ከወዴትኞቹ ነህ? ኪዳኑን፣ማሕሌቱን፣ቅዳሴውን ወንጌሉን ችላ ብለው ሥልጣኔ በሚመስል ኋላ ቀርነት ዕውቀት በሚመስል ድንቁርና ውስጥ ተጠልፈው በዳንኪራና በዝሙት በዘረኝነትና በስግብገብነት ከወደቁት ወገንነህ ወይስ የቤተ ክርስቲያንን ድምጽ ሰምተው በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ተጠልለው በሕጓና በሥርዓቷ ከሚመሩት ከወዴትኞቹ ነህ ወንድሜ ?

. ፪ የቅዳሴ መግቢያ ደውል

ይህ የቅዳሴ መግቢያ ደወል ካህናቱ መሥዋዕቱን አክብረው ከቤተልሔም ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ የሚደወል ደወል ነው። ዲያቆኑ ወደ ቤተልሔም ሂዶ እጅ ነሥቶ ‹‹ተፈሥሒ ኦ ቤተ ልሔም ሀገሮሙ ለነቢያት እስመ በኀቤኪ ተወልደ ክርስቶስ ›› ብሎ ከጸለየ በኋላ ታጥቦ ንጹሕ ሆኖ ‹‹አፍኣዊ እድፌን በውኃ ታጥቤአለሁ ውሳጣዊ በደሌን ግን አንተ በቸርነትህ አንጻኝ›› ብሎ ተማጽኖ  ኅብስቱን በመሶበ ወርቅ ወይኑን በጽዋው አድርጎ ካጠናቀቀ በኋላ ካህኑ እንደ መጣ በመሶበ ወርቅ ያለውን ኅብስት ተሸክሞ ጽዋውን በእጁ ይዞ ካህኑን እየቀደመው ደወሉን ወይም ቃጭሉን እያቃጨለ ‹‹መስቀል አብርሃ፣ኵሉ ዘገብራ ለጽድቅ እና እምነበሐ›› የሚሉ ዜማዎችን እያዜመ ወደ ቤተ መቅደሱ ካህኑን እየቀደመው ይገሰግሳል፡፡ ይህ ሁሉ ምሳሌ ነው መሶብ የእመቤታችን ወርቅ የንጽሕናዋና የቅድስናዋ ምሳሌ ነው፡፡

ዲያቆኑ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ ምሳሌ ሲሆን ካህኑ ደግሞ የመድኃኔዓለም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዲያቆኑ ከካህኑ እየቀደመ ፊት ፊት መሄዱ ዮሐንስ ከክርስቶስ መንፈቅ ቀድሞ ለመምጣቱ ምሳሌ ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የሚደወለው የደወል ድምጽ ሁለት ምሥጢራውያን ትርጉሞች እንዳሉት መተርጉማን  ሊቃውንት ያትታሉ፡፡

አንደኛ የብሥራተ ገብርኤል ምሳሌ፣ መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ምልእተ ጸጋ ምልእተ ክብር ሆይ ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና እያለ የምሥራቹን ነግሯታልና የዚያ ምሳሌ እንደሆነ መተርጉማኑ ያስተምራሉ(ሉቃ ፩፥፳፮)

ኢትዮጵያዊው የነገረ መለኮት ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም መጽሐፈ ምሥጢር በተባለ መጽሐፉ ላይ እንዲህ በማለት የቅዱስ ገብርኤልን አብሣሪነት ይገልጣል፡፡‹‹ወአመ ትስብእተ መለኮቱ ለወልድ ይቤላ ቅዱስ ገብርኤል ለድንግል ማርያም በእንተ መንፈስ ቅዱስ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወበእንተ አብኒ ይቤ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ ወበእንተ ወልድኒ ይቤ ወዘኒ ይትወለድ እምኔኪ ቅዱስ ውእቱ ወይሰመይ ወልደ ልዑል፣ወልድ ሰው በኾነ ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል ስለ መንፈስ ቅዱስ ድንግል ማርያምን መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል ብሎ ነግሯታል፡፡

ስለአብም የልዑል ኃይል ይጋርድ ሻል አላት፡፡ስለወልድም ከአንች የሚወለደው ቅዱስ ነው የልዑል ልጅም ይባላል..ብሎ ቅዱስ ገብርኤል እንዳበሠራት ይናገራል (መጽሐፈ ምሥጢር ገጽ ፻፴፩)

የብሕንሳው ሊቅ አባ ሕርያቆስም እመቤታችንን ባመሰገነበት በቅዳሴው ላይ የቅዱስ ገብርኤልን የምሥራች ነጋሪነት እንዲህ ሲል ይመሰክራል ‹‹ወሶበ ርእየ ንጽሕናኪ ለሊሁ እግዚአብሔር አብ ፈናወ ኀቤኪ መልአኮ ብርሃናዌ ዘስሙ ገብርኤል ወይቤለኪ መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ መጽአ ኀቤኪ ቃል እንዘ ኢይትፈለጥ እምሕጽነ አቡሁ ፀነስኪዮ እንዘ ኢይትጋባእ ተዐቁረ ውስተ ከርሥኪ እንዘ ኢየሐጽጽ በላዕሉ ወኢይትዌሰክ በታሕቱ ኀደረ ውስተ ከርሥኪ እሳተ መለኮት ዘአልቦቱ ጥያቄ ወኢመጠን፣እርሱ ቅሉ እግዚአብሔር አብ ንጽሕናሽን ባየ ጊዜ ስሙ ገብርኤል የሚባል ብርሃናዊ መልአኩን ወደ አንቺ ላከ መንፈስ ቅዱስ በላይሽ ይመጣል የልዑል ኀይልም ይጋርድሻል አለሽ ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ ሳይወሰን ፀነስሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨምር በማሕፀንሽ ተወሰነ መጠንና መመርመር የሌለበት እሳተ መለኮት በማሕፀንሽ ዐደረ›› በማለት በአድናቆት ይገልጻል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም ቁጥር ፵፭) ደወል ቅዳሴ መገባቱን መሥዋዕት የሚሠዋበት ጊዜ መሆኑን እንደሚገልጽ ሁሉ ቅዱስ ገብርኤልም የክርስቶስን መወለድ አብሥሯል፡፡ልደቱም በቤተልሔም ተፈጽሟል፡፡

ሁለተኛ የስብከተ ዮሐንስ ምሳሌ፤ ይህ ደወል መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ተራራው ዝቅ ይበል ጎድጓዳው ይምላ የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውን አስተካክሉ፣እንሆየዓለምን ኃጢአት የሚያስተሰርይ የእግዚአብሔር በግ›› (ማቴ ፫፣ዮሐ ፩፥፳፱) ብሎ የጮኸው ድምጽ ምሳሌ ነው። ይህንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድጓው እንዲህ ሲል ተርጉሞና አብራርቶ ይነግረናል፡

‹‹ኢሳይያስኒ ይቤ ናሁ እፌኑ መልአኪየ ኅቤከ ቅድመ ገጽከ ዘይጸይሕ ፍኖተከ ቃለ ዐዋዲ ዘይሰብክ ጥምቀተ ለንስሓ፣የንስሓን ጥምቀት የሚሰብክ በፊትህ መንገድን የሚጠርግ አዋጅ ጋሪ መልክተኛየን እልካለሁ ብሎ ኢሳይያስ እንደተናገረ››

‹‹ቃለ ዐዋዲ ዘይሰብክ ጥምቀተ ለንስሓ ከመ ይእመኑ ሕዝብ በብርሃኑ ዮሐንስ ክቡር ሰባኬ ቃለ ወንጌል ተፈኖኩ ቅድሜሁ ዐርኩ ለመርዓዊ ሰማያዊ፣ሕዝቡ በብርሃኑ ያምኑ ዘንድ የንስሓ ጥምቀትን የሚሰብክ ዐዋጅ ነጋሪ የተከበረ የወንጌል ሰባኪ የሰማያዊ ሙሽራ ወዳጅ እኔ ዮሐንስ በፊቱ ተላክሁ››

‹‹ ዮሐንስ ካህን ወድንግል እንዘ ይሰብክ ቃለ ወንጌል ወይቤሎሙ ለሐራ ጺሑ ፍኖቶ ለልዑል፣ካህንና ድንግል የሆነ ዮሐንስ የወንጌልን ቃል እየሰበከ ለጭፍሮቹ ወይም ለወታደሮች ለታላቁ ንጉሥ መንገዱን ጥረጉለት ጥርጊያውንም አስተካክሉለት››ሰባኬ ወንጌል ዘጥዑም ልሳኑ ርስነ መለኮት ገሠሠት የማኑ፣ፀጒረ ገመል ተከድነ ዘባኑ ለዮሐንስ ኂሩቶ ንዜኑ፣አንደበቱ የጣፈጠ የወንጌል ሰባኪ ቀኝ እጁ የመለኮትን ግለት ዳሠሠች የዮሐንስ ጀርባ በግመል ፀጉር ተሸፈነ ይህን የዮሐንስን ቸርነት እንናገራለን ›› በማለት ቃለ ዐዋዲ የተባለ ዮሐንስ በስብከቱ የራቁትን እንዳቀረበ የተበተኑትን እንደሰበሰበ ሊቁ በድጓው ነግሮናል፡፡ የደወል ምሳሌም ይህ ነው፡፡

                 ፫ የወንጌል ደወል

  በቅዳሴ ሰዓት ወንጌል ከተነበበ በኋላ ዲያቆኑ “ፃኡ ንኡሰ ክርስቲያን”ብሎ ሲያውጅ የሚደወል ደወል ነው፡፡ ንኡሰ ክርስቲያን የሚባሉት ክፉውን ምግባር በጎ ምግባር፣ ክፉን ሃይማኖት በጎ ሃይማኖት መስሏቸው ይዘውት ሲኖሩ በኋላ ግን ቃለ መምህራንን ሰምተው ክፉውን ትተው ወደ በጎው ከተመለሱ በኋላ ነገረ ሃይማኖት እየተማሩ ወደቤተ ክርስቲያን እየሔዱ የትምህርትና የንባብ ክፍለ ጊዜውን ከተከታተሉ በኋላ ፍሬ ቅዳሴ ላይ ሲደረስ የክርስቲያን ታናናሾች ለዚህ ምሥጢር ያልበቃችሁ ውጡ ሲል ደወል ይደወላል እነርሱም እየወጡ ይሔዳሉ፡፡ ውጡ ሲል የወጡት የኃጥአን ከዚያው ቁመው የቀሩት የጻድቃን ምሳሌ ሲሆን የደወሉ ድምጽ ደግሞ የስብከተ ዮሐንስ፣ የሐዋርያት እና የሰብአ አርድእት ምሳሌ ነው፡፡ ጌታችን ሕገ ወንጌልን ከማስተማሩ በፊት የሰዎችን ልብ ለንስሓ ለማዘጋጅት መንገድ ጠራጊው አዋጅ ነጋሪው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የንስሓ ትምህርት አስተምሯል (ሉቃ ፩፥፴፩)

ቅዱሳን ሐዋርያትም ከዓለም ለይቶ የጠራቸው ጌታችን ሲሰቀል አልቅሰዋል የወንጌል ደወል ከተደወለ በኋላ መሥዋዕት ይሠዋል ሥጋ ወደሙ ተፈትቶ ለሚቀበሉ ይቀርባል እንዲሁም ከመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ የንስሓ ትምህርት በኋላ ጌታችን ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማረ በኋላ በመስቀል ተሰቅሎ ለዓለሙ ድኅነት ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡

                         ፬ የእግዚኦታ ደወል

 በፍሬ ቅዳሴ ላይ ገባሬ ሠናይ ሆኖ ቅዳሴ የገባው ካህንና ተጨማሪ ካህናት እና ምእመናን እየተቀባበሉ ፵፩ ጊዜ “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” ይባላል በዚህን ጊዜ የሚሰማው የደወል ድምፅ የእመቤታችን እና የወንጌላዊው ዮሐንስ የለቅሶ ድምፅ ምሳሌ ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ ሲሰቀል ባዩ ጊዜ  ከእግረ መስቀሉ ሥር ኾነው  አልቅሰዋል (ዮሐ ፲፱፥፳፭)

ዛሬም ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኾነው ‹‹አቤቱ ማረን ይቅርም በለን›› እያሉ ዘወትር ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን ግፍዐ ሰማዕታትን የራሳቸውን በደልና ኃጢአት እያሰቡ ዮሐንስን ምሳሌ አድርገው እንዲያዝኑ እንዲያለቅሱ ይህ የደውል ድምፅ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘወትር ይሰማል።

                      ፭ የድርገት ደወል

ድርገት ማለት አንድነት ኅብረት ማለት ሲሆን ይኸውም ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትናን የታደሉ ምእመናን አንድ ሆነው በአንዲት ቤተ ክርስቲያን የአንዱን የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን የሚቀበሉበት እና  ካህናቱም ሥጋ መለኮትንና ደመ መለኮትን ለማቀበል አንድ ኾነው ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ››እያሉ ከመቅደስ ወደ ቅድስት የሚወጡበት ነውና  ድርገት ተባለ ሲወጡም ደወል ይደወላል፡፡

በዚህን ሰዓት የሚደወለው የደወል ድምጽ የቅዱስ ዮሴፍ እና የቅዱስ ኒቆዲሞስ ለቅሶ ምሳሌ ነው፡፡ እንዲሁም የቅዱሳን ሐዋርያት እና የሰብአ አርድእት ትምህርት ምሳሌ ነው( ሉቃ ፳፫፥፶)

ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጌታን ከቅዱስ መስቀሉ አውርደው እያለቀሱ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት  ዕለት ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ  በስብሐት ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሣሃለነ እግዚኦቅዱስ እግዚአብሔር ፡ቅዱስ ኃያል ፡ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ  ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ  አቤቱ ይቅር በለን፣፣ቅዱስ እግዚአብሔር ፡ቅዱስ ኃያል ፡ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ በዮርዳኖስ የተጠመቀ  በመስቀል የተሰቀለ አቤቱ ይቅር  በለን፣፣ቅዱስ እግዚአብሔር ፡ቅዱስ ኃያል ፡ቅዱስ ሕያው የማይሞት የማይለወጥ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ የተነሣ  በክብር፡ በምስጋና ወደ ሰማይ  ወጣ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ  ዳገመኛም በሕያዋንና በሙታን ለመፍረድ  በጌትነት ይመጣል አቤቱ ይቅር በለን ›› እያሉ በአዲስ መቃብር አኑረውታል፡ (የኪዳን ጸሎት )

ዛሬም የዮሴፍና የኒቆዲሞስ ምሳሌ የሆኑ ካህናት የቀራንዮ ምሳሌ ከሆነው ከመንበሩ አውርደው አፍዓዊ እድፋቸውን በሳሙና ውሳጣዊ በደላቸውን በንስሓ ወልውለው ራሳቸውን አዲስ ባደረጉ በምእመናን ልቡና ውስጥ ይቀብሩታል፡፡ የምእመናን ልቡናም ያንጊዜ መቃብረ ክርስቶስ ይሆናል፡፡ ለዚህ ነው ኦርቶዶክሳውያን ሥጋውን እንደበሉና ደሙን እንደጠጡ አፋቸውን የሚሸፍኑት ፡፡

የመሸፈናቸው ምሥጢርም አንደኛ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጌታን በአዲስ መቃብር ከቀበሩት በኋላ መቃብሩን በድንጋይ የመግጠማቸው ምሳሌ ሁለተኛ ለእኛ ስትል የተቀበልኸው መከራ ከመናገር በላይ ነው ሲሉ፤ ሦስተኛ ክርስቶስ በውስጤ አለ ሲሉ፣ አራተኛ ከአሁን በኋላ ለኃጢአት የተዘጋው በር ነኝ ሲሉ! ስለሆነም ምእመናን የጌታን መከራውን ሥቃዩን ግርፋቱን ሞቱን ትንሣኤውን እያሰቡ በፍርሃት እና በመንቀጥቀጥ ወደ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ይቀርቡ ዘንድ ድርገት ሲወርድ ሁል ጊዜ ደወል ይደወላል፡፡

በመሆኑም በደወሉ ድምጽ የተኛን ተቀስቅሰን የዛልን በርትተን የተለያየን በዓላማ አንድ ሆነን የመንግሥቱ ወራሾች እንሆን ዘንድ አምላከ ቅዱሳን ይርዳን !

 

 

ከኦርቶዶክሳዊ ወጣት ምን እንጠብቅ?

ዲ/ን ታደለ ፈንታው(ዶ/ር)

ክፍል አንድ

 

ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን የደም ዋጋ ተከፍሎበት፤ ተፈትኖ፣ ነጥሮ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግሮ በቅብብሎሽ የመጣ እውነተኛ ሃይማኖት ነው፡፡ የዓለማውያን ፍልስፍና፣ ተረት ተረት፣ ድርሰትም፣ የታዋቂ ሰዎች ድንገተኛ ፈጠራም አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ደም ላይ ተመሥርታለች እና ተጠብቃ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሸጋገርም ወጣቶች የከፈሉት ዋጋ ደማቅ በሆነ በደም ቀለም በቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገበ ነወ፡፡ እንደ ምሳሌም ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን ማንሣት እንችላለን፡፡ ራሱን ለእግዚአብሔር አሳልፎ በመስጠቱ አይሁድ በድንጋይ ሲወግሩት ሰማያት ተከፍተው የእግዚአብሔርን ዙፋን እስከ ማየት አድርሶታል፤ ምሥጢርም ተገልጦለታልና አቤቱ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” እስከ ማለት አደረሰው፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ወጣቶች አርአያ ሊያደርጉት ይገባል፡፡ (ሐዋ. ፯፥፶፬-፷)

ከአባቶቻችን፣ ከእናቶቻችን  የተቀበልነውን ይህንን የደም ዋጋ የተከፈለበትን  እውነተኛ ሃይማኖት እንደ ወጣት በምንኖርበት ዘመን የመጠበቅ፣ የመከላከል፣ የብዙዎች መዳንን የሚሹ፣ በእውነተኛው መንገድ ለመጓዝ የፈቀዱ ሰዎችን እንዲያውቁት፣ እንዲገነዘቡት፣ በሥጋቸውም በነፍሳቸውም እንዲጠቀሙበት ማድረግ የአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ ወጣት የሃይማኖት ግዴታ ነው፡፡ እምነታችንም የሚገለጠው ዕለት ዕለት በማኅበረሰቡ መካከል ስንመላለስ በምናሳየው የማይለዋወጥ ባህርይጥሩ ሥነ ምግባር አማካኝነት ነው፡፡ የእኛ ጽናት፣ አቋም፣ ጥንካሬ፣ መንፈሳዊ ሕይወት የሃይማኖታችንን እውነተኛነት ይገልጣል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ የክርስቶስ መልክ የሚታይበት ሰው ነው፡፡ በክርስቶስም የእግዚአብሔር መልክ በእርሱ ላይ ታትሟልና፡፡

በምንኖርበት ሉላዊ ምድር በዓለም ላይ እንደሚኖር ሰው ተግዳሮቶች አሉብን፡፡ እኒህ ተግዳሮቶች ታስበው ታቅደው እንደሚሠሩ ሁሉ ሰው በመሆናችን፣ ሉላዊውን ዓለም በመጋራታችን  ጭምር የሚመጡ እንጂ ክርስቲያን በመሆናችን ምክንያት ብቻ ተለይተው የሚመጡ አይደሉም፡፡ ክርስትናን ለመቃወም ታስበውም ሆነ ሳይታሰቡ የሚወጡ አፋኝ ሕጎች፤ የሉላዊነት ተጽእኖ፣ ኤችአይቪ ኤድስና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች፤ ድህነት፣ የደኅንነት ስጋት፣ ዘረኝነት፣ ያልተስተካከለ እና ሕይወትን የማያሻሽል መሠረቱን አገር በቀል እውቀትን ያላደረገ የተኮረጀ ትምህርት እና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ መልእክቱ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፡- “እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና ፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፤ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ፤ ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና እርሱም ባልንጀራህን እንደራስህ አድርገህ ውደድ የሚል ነው፡፡  ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና  ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ፡፡” እንዲል(ገላ 5፡13)

ፍቅር የእምነታችን እና ጽናታችን መሠረት

እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ ተከታይ የእምነታችን ታላቅነት የሚገለጠው ለሌሎች በሚኖረን ፍቅር እና አክብሮት ላይ ነው፡፡ ሕግ ሁሉ በሁለት ምሰሶዎች ላይ የቆመ ነው፡፡ እነርሱም ፍቅረ እግዚአብሔር እና ፍቅረ ቢጽ(የወንድም ፍቅር) ናቸው፡፡ ሰው የሚመለከተውን ወንድሙን፣ የሚመለከታትን እኅቱን የማይወድ ከሆነ የማይመለከተውንና ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ እንደምን ይቻለዋል? ስለዚህ ፍቅራችን በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል የቆመች እውነተኛ የሃይማኖታችን መገለጫ ምልክት ናት፡፡ እኛም እውነተኛ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደመሆናችን፤ በቅዱሳት መጻሕፍትም መሠረትነት ላይ ልንጓዝ ግድ ይለናል፡፡

የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገለጫው ፍቅር ደስታ፣ ሰላም፣ ቸርነት በጎነት  የዋህት፣ ራስን መግዛት(ገላ. ፭፥፳፪) እንጂ ዝሙት ርኩሰት ፣ መዳራት፣፣ ጣዖትን ማምለክ ምዋርት፣ ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቁጣ አድመኛነት፣ መለያየት፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት መግደል ስካር ዘፋኝነት (ገላ. ፭፥፳) አይደለምና በቀደሙ በአባቶቻችን የፍቅር መንገድ እንጓዝ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካሙን ሥራችሁን ተመልክተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን ያመሰግኑ ዘንድ ብርሃናችሁ በሰው ሁሉ እንዲሁ ይብራ” እንዳለ(ማቴ ፭፥፲፫) ከውኃና ከመንፈስ ዳግም ስንወለድ ሀብተ ጸጋ ሀብተ ልጅነት ሆነው የተሰጡን መንፈሳውያን ሀብቶቻችን ይገለጡ ዘንድ ብርሃናችን  በዓለሙ ሁሉ ይብራ፡፡ እነዚህም አስቀድመን የገለጥናቸው ናቸው፡፡ ፍቅር የእግዚአብሔር ገንዘብ ነው፡፡ ፍቅር እግዚአብሔርን የምናውቅበት ፍኖት ነው፡፡

ፍቅር እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት፣ ሰው፣ እንስሳ ሳንል የምንወድበት መሳሪያ ነው፡፡ ፍቅር ተፈጥሮአችንን የምናድስበት ነው፡፡ ፍቅር ጉድለታችንን የምንሞላበት መዝገብ ነው፡፡ ፍቅር የተጣመመን ሰብእና የምናርቅበት መዶሻ ነው፡፡ ፍቅርን ተከትለው የሚመጡ ሌሎች ሀብታት አሉ እንጂ ፍቅር ብቻውን የሚመጣ አይደለም፡፡ ፍቅር፡– ሰላምን፣ ደስታን ያስከትላል፡፡ ርኅራኄ እና ለጋስነት ያጅቡታል፡፡ ፍቅር ማደሪያውን ትሕትናን እና ራስን መግዛትን ያደርጋል፡፡

እንደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኝ የሚጠበቅብን ብዙ ነገር አለ፡- አስቀድመን በገለጽናቸው መንፈሳዊ ሀብታት መኖር እና ማደግ ዕድገታችንም ዕለት በዕለት ያለ ድካም፣ ያለ ፍርሃት፣ የሚጨምር ሊሆን ይገባዋል፡፡ እነዚህን ሀብታት ሳንታክት ገንዘብ ልናደርጋቸው የሚገቡ ጠቃሚ ሀብታት ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀብታት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ ክርስቶስን እንለብሰዋለን፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደሶችም ተብለን በእውነት ልንጠራ የተገባን እንሆናለን፡፡

ሌሎች ሊኖሩን የሚገቡ ዕሤተ ምግባራት

እንደ ክርስቲያን በሕዝብ እና በአሕዛብ መካከል የምንመላስ የክርስቶስን እውነት የምንመሰክር ደምቀን የምንታይ አጥቢያ ኮከቦች ነን፡፡ አጥቢያ ኮከብ ደምቆ፣ ፈክቶ እና አብርቶ ስለሚኖር ለሁሉ እንደሚታይ እውነተኛ ክርስቲያንም በሰው ሁሉ ፊት የተገለጠ ነው፡፡ የበለጠ ደምቀን እንድንታይ የሚያደርጉን ኦርቶዶክሳዊ ዕሤተ ምግባራት አሉ፡ እነርሱም፡- አርምሞ፣ ሥርዓት፣ ሰላማዊ ኑሮ፣ ዕውቀት፣ ማስተዋል፤ በሕዝብ ተገብቶ ራስን አሳልፎ መስጠት፣ ከግለኝነት መጽዳት፣ በሰዎች ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት፣ እና እኒህን የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ልንታገሳቸው የማይገቡንም ነገሮች አሉ፡፡ እነርሱም፡- ሞራል ማጣት፣ የነፍስን ቅድስና ገንዘብ አለማድረግ፤ ጣዖትን ማምለክ፣ ጥንቆላ እና ተያያዥ ተግባራትን መውደድ፣ ምቀኝነትን አለመጥላት፣ ጠብንና አምባጓሮን መውደድ፣ ከቁጣ ነጻ አለመሆን፣ በተሰጠን ነገር አለመርካት፣ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማነጻጸር እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አስቀድመን የዘረዘርናቸውን ነገሮች የምንጠላቸው በሥጋችን ሥቃይን የሚጨምሩብን በነፍሳችንም የሚያስጎዱን እንጂ የሚጠቅሙን ባለመሆናቸው ነው፡፡

በእውነት  መንገድ የሚኖር ኦርቶዶክሳዊ ወጣት፡-

በምንመራው ኦርቶዶክሳዊ እውነተኛ ኑሮ ሕይወትን በተወሳሰበ እና ለዓለም በሚመች መልኩ ማድረግ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ እኛ እንድንኖር የተፈቀደልን ሕይወት ጸሎት ያጀበው ሕይወት፣ የፍቅር ሕይወት፣ ለጎረቤቶቻችን ለወንድሞቻችንና እኅቶቻችን መልካም ነገርን የማድረግ ሕይወት ከምንም በላይ ለነፍሳችን ድኅነት የሚጠቅመንን ሥራ የመሥራት ሕይወት ነው፡፡ ንቁ ሆነን፣ አለባሰሳችን እንደ ሃይማታችን ሥርዓት ሆኖ፣ ለጸሎት የነቃን፣ የታጠቅን መሆን ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክን በቃልም ቢሆን በተግባርም ቢሆን በኀልዮም ቢሆን የሠራነውን ኃጢአት ይቅር ይለን ዘንድ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሔር ዘወትር በሥራው ከእኛ ጋር ይሆን ዘንድ ይህ የአንድ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ የዘወትር ጸሎት ነው፡፡ መሻቱም፣ ፈቃዱም ፣ ውዱም ሁሉም ተጠቅሎ ያለው በዚያ ውስጥ ነው፡፡ መነሻውም መድረሻውም የጸሎት እና የምስጋና ሕይወት ነው፡፡

በዚህ መንገድ የሚኖር ኦርቶዶክሳዊ ወጣት፡- ሕይወቱ ለአንድ የተስተካከለ እና ጤናማ ሕብረተሰብ መኖር ምሰሶ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ፍትኅ፣ ደስታ እና ሰላም የሚጠበቀውም በእንዲህ ዓይነት መንገድ አልፈው ማኅበረሰቡን በሚያገለግሉ ወጣቶች እንጂ አፈ ጮሌዎች ፣ ስግብግቦች እና ነገር አዋቂዎች አይደለም፡፡ እንዲህ ዓይነት እዩኝ እዩኝ የሚሉ ከንቱ ሰዎች  ማኅበረሰብን መርተው ወደሚፈልገው ዕድገት  አያሻግሩም፡፡

ሀብት አስፈላጊ ቢሆንም ኦርቶዶክስ ክርስቲያን የሚኖረው ሀብት ለማግበስበስ፣ ሌሎችን ለመቀማት ወይም ለማስቀናት አይደለም፡፡ ሀብትን ከፈለግነው በአባቶቻችን በእናቶቻችን መንገድ በርግጥ በእውነት እና በቅንነት ብንመላለስ   የሚመጣ እንጂ የሚርቅ ነገር አይደለም፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ በመጀመሪያ ጽድቁን እና መንግሥቱን ሹ፤ ሥጋን ለሥጋ ነገር ማለማመድ ለአሁኑ ጊዜ ይጠቅማል፤ ሥጋን ለመንፈሳዊ ነገር ማለማመድ ለአሁኑ ጊዜ ለሚመጣውም ጊዜ ይጠቅማል ይላል፡፡

የሚገጥመን ተግዳሮት

         በመንፈሳዊ ልምምድ ሳለን የሚገጥመን ተግዳሮት ቀላል አይደለም፡፡ ጠላታችን ዙሪያችንን ይዞራል፡፡ ወጥመዱን ይዘረጋል፡፡ የአጋንንትን ትምህርት በሚያስተምሩ ሰዎች ልባችንን ለመክፈል እንዲሠሩ ያደርጋል፡፡ ነገሮች ለእነርሱ አልጋ በአልጋ ሲሆኑ ለጊዜው ሁሉም ነገረ የተሳካላቸው አስመስሎ፤ የሌለ ነገር እንዳለ አድርጎ ማሣየት የአጋንንት ተግባር ነው፡፡ ከእውነተኛው ሃይማኖታችን ለማስወጣት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታይ በመሆናችን ሃይማኖታችንን የድኅነት ምንጭ፣ ስብከታችንንም ከንቱ አድርጎ ሊስል ይዳዳዋል፡፡ በእምነት የቀደሙንን ቅዱሳን፤ አሠረ ፍኖት ትተውልን የሄዱ ዋኖቻችንን ድካም ከንቱ ድካም አድርጎ ለመሳል የማይሄድበት ርቀት የለም፡፡ ረብህ የሌላቸውም ምናምንቴ ሰዎች በገበያ እና በፕሮሞሽን ወደፊት አውጥቶ ሰዎች እንዲከተሏቸው ያደርጋል፡፡ የዲያብሎስ ወጥመዱ ብዙ ነው፡፡

የቅዱስ ጳውሎስ ምክር “በቃልና በኑሮ በፍቅርም  በእምነትም በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን እንጂ  ማንም ታናሽነትህን አይናቀው፤ እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ፡፤( ፩ኛ ጢሞ. ፬፥፲፪) የሚል ነው፡፡ ፍቅራችን፣ ራስን መግዛታችን   በቃልም በኑሮም ከተገለጠ የወጣትነት ሕይወታችን እጅግ ጣፋጭ፣ ተወዳጅ እና ፍሬ የሚያፈራ ይሆናል፡፡ በእንዲህ ዓይነት የተቀደሰ ሕይወት ስንመላለስ ፈተና ቢገጥመን  ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል የተቀበላቸው በርከት ያሉ መከራዎችን እናስብ፡፡ እርሱን በመልበሳችን ምክንያት ወደ እኛ የመጡ መከራዎች መሆናቸውን በማሰብ ዕለት ዕለት በፈተና እንጸና ዘንድ ሳናቋርጥ እንጸልይ፡፡  ጸሎታችንም መንፈሳዊ  ድፍረትን፣ ጥበብን ፣ ማስተዋልን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ፍቅርን፣ ትሕትናን በጎ ጤንነትን፣ ሀብትን፣ ረጅም የአገልግሎት ዕድሜን ይሰጠን ዘንድ ነው፡፡ ይቆየን፡፡

 

ልደተ ክርስቶስ

መ/ር በትረ ማርያም  አበባው

 

የሰው ልጅ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስን በልቶ  በራሱ ላይ ሞትን ዐወጀ ከእግዚአብሔር ተለየ (ዘፍ. ፪፣፲፯) ቸርነት የባሕርየ  የሆነ እግዚአብሔር ግን ሰውን ሞቶ እንዲቀር አላደረገውም። በከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ኪዳን ሰጠው። እግዚአብሔር ይህንን ቃል ኪዳን በየዘመኑ ለተነሡ ሰዎች በተለያዩ ነቢያት አስነገረ።

       “ ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ እምርላሃለሁ፣ይቅርታም አድርግልሃለሁ “(ቀሌም.፫፥፲፱፣ኢሳ.: ኢሳ.፱፣፮) እንዲል  ጊዜው  በደረሰ ጊዜም ከሦስቱ አካላት እግዚአብሔር አንዱ ወልድ ከድንግል ማርያም ተወለደ። “ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ” እንዲል (ማቴ. ፩፣፳፩-፳፫፣ሉቃ. ፪፣፮-፯፣ዮሐ. ፩፣፲፬ ፣ገላ. ፬፣፮)

  ጌታችን ሁለቱ ልደታት

ጌታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት።እኒህም ቀዳማዊ ልደትና ደኃራዊ ልደት ይባላሉ።

                         ቀዳማዊ ልደት

አብ ወልድን በዘመን ሳይበልጠው የወልድ ቃልነት የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሳይለየው ወልድን ወለደው መንፈስ ቅዱስን አሠረፀው እንላለን። ይህም ከኅሊና በላይ የሆነ በሰውና በመላእክት አእምሮ ሊመረመር የማይችል  ነው። “ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድኩህ” (መዝ. ፻፱፣፫)  እንዲል። ስለዚህም የአብ  ግብሩ ወላዲ ይባላል። የወልድ ግብሩም  ደግሞ ተወላዲ ይባላል። በቀዳማዊ ልደቱ እናት የለውም። ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ “ከመዝ ነአምን ዘአልቦቱ እም በሰማያት” ብሎ የገለጸው ይህንን ነው። በዚህኛው ልደት ተመትሮ የለበትም። ይህም ማለት አብ ወልድን ሲወልደው ወልድ ከአብ አልተለየም።  ዘኢየኀልቅ ልደቱ ያሰኘው ይህ ነው። ወልድ ወልድ ሲባል ይኖራልና።

                            ደኃራዊ ልደት

    ደኃራዊነቱ ለቀዳማዊው ልደት ነው። በኋለኛው ዘመን አዳምን ለማዳን ያለ አባት ከድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ነው። ይህ ልደት ያለ ወንድ ዘር፣ያለ ሩካቤ ከድንግል ማርያም የተወለደው ልደት ነው። በክርስቶስ ልደት የሰው ልጆች ተስፋ ተፈጸመ። ስለዚህም እረኞች ከመላእክት ጋር የደስታ ምስጋናን አመሰገኑ። “ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ። ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር። ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ”  (ሉቃ. ፪፣፲፫-፲፬ )  እንዲል ለምድር ሰላም ተሰበከላት። ሰላሟ ክርስቶስ መጣ። እሾህ አሜኬላ ይብቀልብህ ፍትወታት እኩያት ይሰልጥኑብህ የተባለ ሰው በክርስቶስ ልደት ግን “በጎ ፈቃድ ሆነለት” ። ድንግል ፈጣሪዋን በሥጋ ወለደችው። (ሃይ. አበ. ፵፯፣፪-፬)

                        እንዴት ሰው  ሆነ

       እግዚአብሔር  ወልድ ሰው ሲሆን እግዚአብሔርነቱን ሳይለቅ ያለ መለወጥ ነው። እግዚአብሔር የሚለዋወጥ አምላክ አይደለምና። ሰውም አምላክ ሲሆን ሰውነቱን ለውጦ አይደለም። ሰው አምላክ ሆነ እያልን ስንናገር ስለክርስቶስ ሰውነት እየተናገርን መሆኑን ማስተዋል ይገባል። አምላክ ሰው ሆነ ስንልም በተለየ አካሉ ስለ አካላዊ ቃል  ወልድ  እየተናገርን መሆኑን መረዳት ይገባል።

አብ እና መንፈስቅዱስ ሰው አልሆኑምና። ከዊነ ልብ እና ከዊነ እስትንፋስ ሰው አልሆኑምና። ቃል ሥጋ ሲሆን ሥጋም ቃልን ሆነ። የቃል ገንዘብ የሆነው ሁሉ ለሥጋ ሆነ። የሥጋ ገንዘብ የሆነው ሁሉ የቃል ሆነ። ቅዱስ ቄርሎስ እንደተናገረው። “እንቲኣሁ ለቃል ኮነ ለሥጋ ወእንቲኣሁ ለሥጋ ኮነ ለቃል”። የኢየሱስ ክርስቶስን ልዕልናውን በትሕትናው አወቅን። ስለዚህ ያለ መለወጥ፣ ያለ መቀላቀል፣ ያለ መለየት በተዋሕዶ በተዐቅቦ ሰው ሆነ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ከፊት ይልቅ ትጉ (፪ኛ.ጴጥ. ፩፥፲)

በመጋቤ ሃይማኖት መ/ር  ምትኩ አበራ

ይህንን ኃይለ ቃል የተናገረው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ነው፡፡ ኃይለ ቃሉን የምናገኘው ደግሞ በ፪ኛ ጴጥ.፩፥፭-፲፩ ላይ ነው፡፡ ሙሉው ንባብ እንዲህ ይላል፡- “… ስለዚህ ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፤ በበጎነትም ዕውቀትን፤ በዕውቀትም ራስን መግዛት፤ ራስንም በመግዛት መጽናትን፤ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፤ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፤ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ፤ እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያድርጉአችኋልና፡፡ እነዚህ ነገሮች የሌሉት ዕውር ነውና በቅርብ ያለውን ብቻ ያያል የቀደመውንም ኃጢአቱን መንጻት ረስቷል፡፡ ስለዚህ ወንድሞች ሆይ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ …”

ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በጥሞናና በእርጋታ ካነበብን በኋላ መልእክቱን በጥልቀት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ርእሱን እናስተውል “ከፊት ይልቅ ትጉ” ነው የሚለው፡፡ እንደ እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ በዚህ ርእስ ሦስት ነገሮችን ብቻ እናያለን፡፡ እነርሱም፡-

፩. ከፊት ይልቅ ትጉ የተባሉት እነማን ናቸው?

፪. ከፊት ይልቅ ትጉ የተባልንባቸው የትጋት አቅጣጫዎች ምንድናቸው?

፫. የተባልነውን በማድረጋችን የምናገኘው ምንድነው? የሚሉት ናቸው፡፡

፩. ከፊት ይልቅ ትጉ የተባሉት እነማን ናቸው?

ኃይለ ቃሉን በአስተውሎት ስንመለከተው ትጉ ብቻ ሳይል “ከፊት ይልቅ ትጉ” ነው የሚለው፡፡ ይህ ማለት ከትጋት በአፍአ ሆነው የሚያንቀላፉትንና በስንፍና ሰንሰለት ታስረው በተስፋ መቁረጥ ምንጣፍ የተኙትን አይመለከትም ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት በትጋት ውስጥ ሆነው የአቅማቸውን እያከናወኑ ላሉት ትጉኀን ክርስቲያኖች የተነገረ ነው ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ትጋታቸውን ተቀብሎና አክብሮ ነው የሚጽፍላቸው ትጋታችሁ ጥሩ ነው፣ ግን ብቻውን በቂ አይደለም ይላቸዋል፡፡ አሁን በትጋታቸው ላይ ትጋትን እንዲጨምሩ ቀድሞ ከነበራቸው ትጋት በተጨማሪ የበለጠ እንዲተጉ ሲመክራቸው “ከፊት ይልቅ ትጉ” ይላቸዋል፡፡ ይህም ማለት ቀድሞ ይጾሙ፣ ይጸልዩ፣ ያገለግሉ ከነበረበት ትጋታቸው በተጨማሪ የበለጠ እንዲተጉ ይመክራቸዋል ማለት ነው፡፡

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እኛስ እንዴት ነን? እየጾምን ነው? በጸሎታችንስ እንዴት ነን? የማያቋርጥ የዕለት ተዕለት ጸሎት ይኖረን ይሆን? እንዲያው ለመሆኑ ከፊት ይልቅ እየተጋን ነው? ወይስ ከነአካቴው በመንፈሳዊ አገልግሎታችን ዝለናል? ምላሹ የራሳችሁ ሆኖ ለራሳችሁ ነው፡፡ ይኼኔ እኮ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከፊት ይልቅ ትጉ እያለ እንኳንስ ከፊት ይልቅ ልንተጋ መደበኛውንና የሚጠበቅብንን ክርስቲናዊ ግዴታችንን እና የአገልግሎት ድርሻችንን በአግባቡ መወጣት የተሳነን ሞልተናል፡፡ ብቻ ፈጣሪ ለሁላችንም ልቡና ይስጠን፡፡

፪. ከፊት ይልቅ ትጉ የተባልንባቸው የትጋት አቅጣጫዎች ምንድናቸው?

እጅግ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ አንባብያን እስቲ አንድ ጊዜ ቀና በሉና ወደ መነሻ(መሪ) ምንባባችን ተመለሱ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በቁጥር ፲ ላይ “…መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ተጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ…” ብሎ ከመጀመሩ በፊት ከላይ እንድናነባቸውና እንድንተጋባቸው የሚያስፈልጉ ዋና ዋና ጉዳዮችን በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ስምንት ሲሆኑ፤ እነርሱም፡-

፩. እምነት                           ፭. መጽናት

፪.በጎነት                              ፮. እግዚአብሔርን መምሰል

፫. ዕውቀት                           ፯. የወንድማማች መዋደድ

፬. ራስን መግዛት                 ፰. ፍቅር ናቸው፡፡

እያንዳንዱ ክርስቲያን እነዚህን ሰፍሮና ቆጥሮ ዘወትር በሕይወቱ ውስጥ እየፈለገ ምን አለኝ? ምንስ ይቀረኛል? በማለት በትጋት እያሰላ መኖር ይገባዋል፡፡

በአርባና በሰማኒያ ቀን ከሥላሴ የጸጋ ልጅነትን ገንዘብ ያደረገ አንድ ክርስቲያን በቅድሚያ እምነት ሊኖረው ግድ ነውና ሐዋርያው በእምነት ጀመረ፡፡ እምነት ወይም ሃይማኖት ስንል ልክ እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት አስፈላጊ ገጽታዎችን የያዘ መሆኑን ማወቅና መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እነሱም ማመንና መታመን ይባላሉ፡፡ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖት ወይም እምነት አለኝ ሲል በፈጣሪዬ አምናለሁ እታመንማለሁ ማለቱ ነው፡፡ ማመን ማለት ለዚህች ዓለም ሠራዒ ወመጋቢ አላት ብሎ ማመን ሲሆን መታመን ማለት ደግሞ አለ ብለን ለምናምነው አምላክ መገዛት፣ እሺ በጀ ማለት በሕጉና በትእዛዙ መጓዝ ማለት ነው፡፡ በጥቅሉ ሃማኖትና ሥነ ምግባርን ይዞ መገኘት ማለት ነው፡፡

የአንድ ክርስቲያን እምነቱ በየጊዜው ያድጋል፡፡ ይህ ማለት የማመኑና የመታመኑ ጥበብ እየተረዳው (እየገባው) ሲመጣና ራሱን ለፈጣሪና ለሕጉ ማስገዛት ሲጀምር ማመኑና መታመኑም እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ስለዚህ ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፣ …” ብሎ ከእምነት የጀመረው፡፡ ሰው አማኝ ሆኖ የበጎነት ድርቅ ካጠቃው ደግሞ ዋጋ የለውም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለምሳሌ በአጽዋማት ጊዜ ውሎ ቅዳሴ እያስቀደሱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይህ እኔ የምቆምበት ቦታዬ ነው እያሉ በቦታ የሚጣሉ ከሆነ እምነታቸው በውስጡ በጎነትና ቅንነት ይጎድለዋል ማለት ነው፡፡

አንዳንዱ ደግሞ በጎነት ይኖረውና በጎነቱ ግን ያለ ዕውቀት ሆኖ ይጎዳዋል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች በበጎነታቸው ገንዘባቸውንና ዕውቀታቸውን የቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት ለማፍረስ ለቆሙ መናፍቃንና የውስጥ ጠላቶች ሲያውሉ ይታያል፡፡ ባለማወቅ የረዱ እየመሰላቸው ማለት ነው፡፡ በረከታቸው ይድረሰንና በአንድ ወቅት የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ “ሃይማኖት ያለ ዕውቀት ጅልነት ነው፤ ዕውቀት ያለ ሃይማኖት እብደት ነው” ይሉ ነበር፡፡ ስለዚህ ነው ሐዋርያው “በእምነታችሁ ላይ ዕውቀትን ጨምሩበት” ያለው፡፡

በዕውቀት ላይ ደግሞ ራስን መግዛት እንድንጨምር ታዘናል፡፡ ምክንያቱም በራስ መግዛት መሪ ያልተዘወረ ዕውቀት የዲያብሎስ ዕውቀት ነው፤ ያስታብያል፣ ወደ እንጦሮጦስም ያስወርዳል፡፡ በራስ መግዛት ላይ መጽናትን ጨምሩበት ካላ በኋላ እንደገና በመጽናት ላይ እግዚአብሔርን መምሰል ጨምሩበት ይለናል፡፡ አንዳንድ ሰዎች “እኔ እግዚአብሔርን ብሆን ኖሮ እንዲህና እንዲያ አደርግ ነበር” እያሉ ሲዝቱ ይስተዋላል፡፡ እግዚአብሔርን መሆን ለመፍለጥና ለመቁረጥ ወይም ለማጥፋትና ለመቅሰፍ ብቻ የሚመስላቸው ናቸው፡፡ ግን እኮ እግዚአብሔርን መሆን ውስጥ በጥፊ መመታትና መሰቀል መሸከምም አለ፡፡ ኧረ እንደውም “የማያውቁትን ያደርጋሉና ይቅር በላቸው” ማለትም አለበት፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን መምሰል ማለት ሆደ ሰፊ፣ ነገር አላፊ፣ ይቅር ባይ፣ ቻይና ታጋሽ መሆን ስለ ሌሎች ራስን አሳልፎ መስጠት ማለት መሆኑን ልብ ልንል ያስፈልጋል፡፡ እስኪ ቆም ብለን ራሳችንን እንመርምር፡፡

ሐዋርያው አላበቃም እግዚአብሔርን በመምሰል ላይ የወንድማማች መዋደድን ጨምሩበት ማለትም የሰፈሬ፣ የመንደሬ፣ የእናትና አባቴ … ከሚለው የወጣ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን መሠረት ያደረገ ወንድማማችነትን ገንዘብ አድርጉ ማለቱ ነው፡፡ በዚህ የወንድማማች መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ ይለናል፡፡ ፍቅር ምንድነው? ፍቅር እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔርን ምስክር ያደረገ ከሸፍጥና ከጨለማ ሥራ የጸዳ፣ ፍቅርን ያዙ ሲለን ነው፡፡ አንድም ፍቅር በቅዱስ ጳውሎስ አስተምህሮ (፩ኛቆሮ. ፲፫) የሚታገሰውን፣ የማይቀናውን፣ የማይመካውን፣ የማይታበየውን፣ የማይበሳጨውን፣ ከእውነት ጋር ደስ የሚለውን ቸርነት የሚያደርገውን፣ … ንጹሑን ፍቅር ገንዘብ አድርጉ ይለናል፡፡

የተወደዳችሁ አንባብያን እነዚህን ከላይ የተዘረዘሩትን ስምንቱን ዋና ዋና ቁም ነገሮች ሁል ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ እንፈልጋቸው፤ ጨምሩ እየተባልን አንዱን ይዘን ለሌላው እንድንተጋ ታዘናል፡፡ እስኪ ቆም ብለን እናስብ፡፡ በእያንዳንዳችን ሕይወት ከስምንቱ ስንቱ አሉ? ስንቱን ይዘን ስንቱ ይቀረናል? እነዚህ የክርስትናችን ትጋት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የመንፈሳዊ አገልግሎታችን ማኅቶታት(መብራቶች) ናቸው፡፡ ስለዚህ ዘወትር በትጋት እንፈልጋቸው፡፡ አንዱን በአንዱ ላይ ለመጨመር እንትጋ ፈጣሪያችን መትጋትን ያድለን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

. የተባልነውን በማደረጋችን የምናገኘው ምንድነው?

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ አንባብያን እንግዲህ ከላይ እንዳስቀመጥነው ስምንቱን የትጋት አቅጣጫቻዎቻችንን ተከትለን ባለን የቀድሞ ትጋታችን ላይ እነዚህን ገንዘብ ለማድረግ ዘወትር በትጋት ላይ ትጋት እያሳየን ከቀጠልን ምን እንደምናተርፍ ሐዋርያው በአጭር አገላለጥ አስቀምጦልናል፡፡ እንዲህ ሲል “እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዕውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና”(ቁ.፰)፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ስምንቱን ቁም ነገሮች እየጨመርንና እያበዛን ከሄድን ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንደማንሆን በግልጽ ቋንቋ ነግሮናል፡፡ ሥራ ፈትና ፍሬ ቢስ የሚሉት ቃላቶች ሁለት ቢሆኑም ግን አንድ ናቸው፡፡ አንዱ አንዱን ይስበዋል፤ ማለትም ሰው ሥራ ፈት ሲሆን ነው ፍሬ ቢስ የሚሆነው፡፡ ፍሬ ያለ ሥራ እንደማይገኝ ሁሉ ፍሬ ቢስነትም ያለ ሥራ ፈትነት አይኖርም፡፡

ሥራ ፈትነት በሁለቱም ዓለማት ከባድ ቢሆንም በተለይ በመንፈሳዊው ዓለም ትንሽ ለየት ይላል፡፡ “ሥራ የፈታ አእምሮ የሰይጣን ቤተ ሙከራ ይሆናል” የሚል አባባል አለ፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ.፲፪ ላይ እርኩስ መንፈስ ከሰው እንደሚወጣ (ማውጣት እንደሚቻል) ይነግረንና በዚያው ምዕራፍ ላይ “ተመልሶ ይመጣል” ይለናል፡፡ ይህንን የሐዲስ ኪዳን መተርጉማን ሲያብራሩት ከወጣ በኋላ ተመልሶ የማደር ሥልጣን የለውም ዳሩ ግን ማሰቡ አይቀርም፡፡ ሲያስብ ግን ያ ሰው ከጾም ከጸሎት በአፉ ሆኖ ከመንፈሳዊ ሕይወቱ ከመልካም ሥራው ተዘናግቶ(ተታሎ) ቢያገኘው፡- እንዲህ ይለናል፡፡ “…ወደወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል፤ ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የክፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወሰዳል፤  ገብተው በዚያ ይኖራሉ፡፡ ለዚያ ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል …” (ማቴ.፲፪፥፵፬-፵፭)፡፡

እንግዲህ ልብ አድርጉ የሥራ ፈት አእምሮ ለሰይጣን የተጠረገና ያጌጠ ቤቱ መሆኑን እየነገረን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥራ ፈቶች ብዙ ይነግረናል፡፡ ሥራ ፈቶች የራሳቸውን ነፍስ ከማስኮነን አልፈው ለሌሎች ሰዎችም ጭምር አዋኪዎች ናቸው፡፡ አይሁድ እንኳን በአቅማቸው የሚፈልጉትን ተንኮል ከግብ ለማድረስ ሥራ ፈቶችን ይጠቀሙባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስን በተቃወሙት ጊዜ እነዚህኑ ሥራ ፈቶች እንደተጠቀሙባቸው  መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ “… አይሁድ ግን ቀንተው ከሥራ ፈቶች ክፉ ሰዎችን አመጡ፣ ሕዝቡንም ሰብሰው ከተማውን አወኩ” (ግ.ሐዋ.፲፯፥፭)፡፡

በዚህ በሥጋዊው ዓለም እንኳን ክፉ ሰዎች የክፋታቸውን ጥግ ለመግለጥና ለማሳየት በፈለጉ ጊዜ የሚጠቀሙባቸው እነዚህኑ ሥራ ፈቶችን ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓለምም ቢሆን በተቻለን መጠን ሥራ ፈት ላለመሆን መትጋት አለብን፡፡ ሥራ ማለት ከቀጣሪው አካል የምንታደለው ብቻ ግን አይደለም፡፡ ራሳችን ለራሳችን ሥራ ልንሰጠው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማነበብ፣ መጠየቅ፣ ለመረዳት መጣር ገዳማትንና አድባራትን እየሄዱ እጅ መንሳት፣ ማስቀደስ፣ በሰርክና በልዩ ልዩ የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብራት ላይ እየተገኙ መማር በሰንበት ት/ቤትና በመንፈሳዊ ማኅበራት ውስጥ ማገልገል … ወዘተ፡፡

የተወደዳችሁ አንባብያን ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከላይ ያስቀመጣቸውን ስምንት ቁም ነገሮች በመሰብሰብ ከተጠመዳችሁ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች አትሆኑም ብሎናል፡፡ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች ካልሆንን ደግሞ የሰይጣን መፈንጫ አንሆንም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ከሆንን ደግሞ በመጨረሻ ጊዜ በኃጥአን ሊፈርድባቸው፣ ለጻድቃን ሊፈረድላቸው የሚመጣው አምላካችን “ሑሩ እምኔየ ሳይሁን ንዑ ሀቤየ ቡሩካኑ ለአቡዬ፤ እናንት የአባቴ ቡሩካን ኑ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያዘጋጀሁላችሁን መንግሥተ ሰማያትን ውረሱ” ይለናል፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ከፊት ይልቅ እንትጋ፡፡

ትጉኁ አምላካችን ትጋቱን ያድለን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን፡፡

‹‹በመስቀሉ አርኀወ ገነተ፤ በመስቀሉ ገነትን ከፈተ›› ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ

በመ/ር ለይኩን አዳሙ ባሕር ዳርማእከል
የመጨረሻው …ክፍል -፬
፰.መስቀል በኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ሀገራችን ከቤተ እስራኤል ቀጥላ እግዚአብሔርን በማምለክ ከሌሎቹ ሀገራት ቀዳሚ እንደሆነች ታሪክ ያስረዳል፡፡ ሌሎቹ ሀገራት ለጣዖት ሲሰግዱ ሲንበረከኩ መሥዋዕት ሲሠው ኢትዮጵያ ሀገራች ግን በሦስቱም ሕግጋት (በሕገ ልቡና፣በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል) እግዚአብሔርን በማምለክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እያቀረበች ብሉይን ከሐዲስ አንድ አድርጋ ይዛ ኑራለች፡፡ ወደ ፊትም በዚህ መልካም ሥራዋ ጸንታ ትኖራለች፡፡ ኢትዮጵያ አምልኮተ ጣዖትን ተጸይፋ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ዘርግታ የምትማጸን በመሆኗ እስትንፋሰ እግዚአብሔር የኾነው ቅዱስ መጽሐፍ ክብሯን ከፍ በማድረግ ከ፵ ጊዜ በላይ የከበረ ስሟን ለዓለም ሕዝብ ያስተዋውቃል፡፡
ኢትዮጵያ ባላት የሃይማኖት ጽናት የክርስቲያን ደሴት፣ ሀገረ እግዚአብሔር፣ ምዕራፈ ቅዱሳን ተብላ ትጠራለች፡፡ የክርስቲያን ደሴት ሀገረ እግዚአብሔር ከመባሏም በላይ የእግዚአብሔር ቸርነት ያልተለያት የበረከትና የረድኤት ሀገር ናት፡፡ የበረከት ሀገር የክርስቲያን ደሴት እንድትባል ያደረጋት የቃል ኪዳኑን ታቦትና የዓለም ቤዛ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ዓለሙን ያዳነበትን ሥጋውን የቆረሰበትን ክቡር ደሙን ያፈሰሰበትን ግማደ መስቀሉን ይዛ በመገኘቷና ባላት የሃይማኖት ጽናት ነው፡፡

፱ .ግማደ መስቀሉ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ መጣ?
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የመጣው በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ታሪክ ይናገራል የመጣበትም ምክንያት በሀገራችን በተደጋጋሚ ረኀብ በሽታ ተክሥቶ ስለ ነበር በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ ዳዊት ረኀብና በሽታው እንዲቆም ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ችግሩ ሊወገድ የሚችለው የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ሲመጣ እንደሆነ በራእይ ነገራቸው፡፡ ንጉሡም ወደ ኢየሩሳሌም ቅድስት ዕሌኒ አስቆፍራ ካስወጣችው ከጌታ ግማደ መስቀል ከፍለው እንዲልኩላቸው ለገጸ በረከት የሚሆን ብዙ ወርቅ እና አልማዝ አስጭነው ወደ ኢየሩሳሌሙ ፓትርያሪክ ላኩ፡፡
ፓትርያሪኩ መልእክቱን ተቀብሎ የመስቀሉን ክፋይ አክሊለ ሦክ ቅዱስ ሉቃስ የሣላትን የእመቤታችን ምስለ ፍቁር ወልዳን ሥዕለ አድኅኖ ጨምረው ላኩላቸው፡፡ መልክእተኞችም ይህን ተቀብለው የሲና በረሃ አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከመግባታቸው በፊት የክብር አቀባበል ሊያደርጉላቸው ሲሄድ የተቀመጡበት ባዝራ ጥሏቸው በክብር ዐረፉ እርሳቸው ቢሞቱም በኢትዮጵያውያን ጀግኖችና በልጃቸው በዘርዐ ያዕቆብ ጥረት በጌታ ፈቃድ ግማደ መስቀሉ ወደ ሀገራች ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፡፡ መጥቶም የኢትዮጵያን ምድር ተዟዙሮ ከባረከ በኋላ መቀመጫውን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል በራእይ ገለጸላቸው ‹‹አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀለኛ ቦታ አስቀምጥ›› ካላቸው በኋላ አፈላልገው ቦታውን አግኝው አሁን ካለበት ቦታ ላይ በወሎ ክፍለ ሀገር በግሸን አንባ ወይም ደብረ ከርቤ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ሠርተው በክብር አስቀምጡት፡፡ ከዚያ ዕለት ጀምረው ብዙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቦታው ድረስ ሄደው መስቀሉን ተሳልመው ቦታውን ረግጠው በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ሲያገኙ ኖረዋል ወደ ፊትም ይኖራሉ፡፡

                                                         ፲. የደመራው ምሥጢር
ደመረ ሰበሰበ አከማቸ አንድ ላይ አደረገ በአንድነት አቆመ ማለት ሲሆን ደመራ ማለት ደግሞ መደመር አንድ ማድረግ ማቆም ማለት ነው፡፡ ይህም ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ያሳየናል፡፡
አንደኛ በዓለ መስቀልን ለማክበር ከአራቱም አቅጣጫ በአንድነት ከታናሽ እስከ ታላቅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የተሰበሰቡትን የቆሙትን ኦርቶዶክሳውያን ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ለመስቀል በዓል ከመድረሱ ፊት ከጫካ ተቆርጦ ተለቅሞ ተሰብስቦ መጥቶ እርጥቡ ከደረቁ፣ ደረቁ ከእርጥቡ በአንድነት ተሰብስቦ የሚቆመውን የደመራ እንጨት ያመለክታል፡፡
በእኛ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ደመራ የሚከመርበት ምክንያት ቅድስት ዕሌኒ የተቀበረውን መስቀል ከማውጣቷ በፊት እንጨት ከምራ ወይም ጨምራ ስለነበረ ያን አብነት በማድረግ በዓለ መስቀልን ለማክበር እንጨት እንጨምራለን እንከምራለን፡፡ በደመራው ፊት ለፊት ካህናቱ ጸሎተ አኮቴት ጸሎተ ምሕላውን ከጨረሱ በኋላ በዲያቆኑ ምስባኩ ከተሰበከ የዕለቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላና ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቶ የተደመረውን ደመራ ሊቃውንቱ ‹‹መስቀል አብርሃ በከዋክብት አሠርገወ ሰማየ እምኵሉሰ ፀሐየ አርአየ እያሉ ደመራውን ይዞራሉ፡፡ ምእመናኑም ‹‹እዮሃ አበባየ መስከረም ጠባየ›› እያሉ ምእመናን በዕልልታና በዝማሬ ደመራውን እየዞሩ በተመረጡ አባቶች ይለኮሳል፡፡ የደመራው እንጨት ነዶ ከአበቃ በኋላ የተጸለየበትና በአባቶች የተባረከ ስለሆነ ምእመናኑ ወደ ቤታችው ይወስዱታል ሰውነታቸውን ይቀቡታል ልጆቻቸውን ከክፉ መንፈስ እንዲ ጠብቅላቸው ከአንገታቸው ላይ ያሥሩታል፡፡
    ፲፩. መስቀሉ ለኦርቶዶክሳውያን
ቅዱስ የሆነው የእግዚአብሔርን መስቀል ያላመኑበት ሰዎች አይጠቀሙበትም፡፡ የምናምንበት እኛ የተዋሕዶ ልጆች ግን ከሕይወታችን ጋር የተሳሰረ ከደማችን ጋር የተዋሐደ በልቡናችን ውስጥ ሥር የሰደደ ነው፡፡ ይህንን ስንልም ከአእምሮአችን አንቅተን ከልቡናችን አመንጭተን አይደለም፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገን ነው እንጂ፡፡ ስለሆነም፡-
     ፩ኛ. ቅዱስ መስቀል ለኦርቶዶክሳውያን አጥር ነው፡-አጥር ከዘራፊ ከቀጣፊ ከወራሪ እንደ ሚከለክል ሁሉ ቅዱስ መስቀልም ከሰይጣን ደባ ከአጋንንት ድብደባ የሚከላከል አጥር ነው፡፡ ይህንም ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል ይገልጻል ‹‹መስቀል ምጽንዓተ ቅጽርነ መስቀል ፀሐይ ሠርጐ ነገሥት ሠናይ፤ መስቀል የአንባችን ማጽኛ አጥር ነው መስቀል የተወደደ የነገሥታት ሽልማት ነው፡፡ መስቀል ፀሐይ ነው፡፡›› በማለት ለሰው ልጆች ሁሉ አጥር መሆኑን ገልጧል፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች የመስቀሉን አጥርነትና ኃይል አምነን እንዲህ በማላት ዘወትር ይማጸናሉ ‹‹መስቀል ኃይልነ መስቀል ጽንዕነ መስቀል ቤዛነ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ›› በማለት መስቀሉ አጥር ቅጥር መሆኑን እንመሰክራለን፡፡
    ፪ኛ. ቅዱስ መስቀል ለኦርቶዶክሳውያን መመከቻና ጠላትን ማጥቂያ ነው፡- አባቶቻችን ጠላት ሲነሣባቸው ፈተና ሲገጥማቸው በመስቀሉ ኃይል ተመክተው ድል ያደርጉ ነበር፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ዕንዚራ የሆነው ቅዱስ ያሬድ የቅዱስ ዳዊትን ቃል መነሻ አድርጎ በዜማ ድርሰቱ ላይ እንዲህ ሲል ይዘምራል ‹‹ብከ ንወግኦሙ ለኵሎሙ ፀርነ ይቤ ዳዊት በመንፈሰ ትንቢት በእንተ ዝንቱ ዕፀ መስቀል ዘተሰቅለ ዲቤሁ ቃለ አብ ወበስምከ ነኀሥሮሙ ለእለ ቆሙ ላዕሌነ ወካይበ ይቤ ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ ከመ ያምስጡ እምገጸ ቅስት ወይድኃኑ ፍቁራኒከ ወንሕነኒ ንትፈሣሕ ዮም ወንግበር በዓለ በዛቲ ዕለት፤ዳዊት በትንቢት መንፈስ ጠላቶቻችን ሁሉ በአንተ እንወጋቸዋለን በዚህ ዕፀ መስቀል ላይ የተሰቀለ የአብ አካላዊ ቃል ነው፡፡በላያችን ላይ የቆሙትን በስምህ እናጎሳቁላቸዋለን ዳግመኛም ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠኻቸው ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ እኛም በዚች ዕለት ደስ ይበለን በዓልንም እናድርግ አለ›› በማለት እግዚአብሔርን ለሚፈሩና ለሚያመልኩ የጠላት መመከቻና ማጥቂያ እንደሆነ አስረግጦ ተናግሯል፡፡
በገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ተጽፎ እንደምናገኘው ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ከመክስምያኖስ ጋር ጦርነት በገጠመ ጊዜ ሊሸነፍ ሳለ በሰማይ በፀሐይ ብርሃን ላይ ተቀርጾ በራእይ ‹‹በዚህ መስቀል ጠላትህን ድል ታደርጋለህ›› የሚል ጽሑፍ አነበበ ቆስጠንጢኖስም ሳይጠራጠር በመስቀሉ ኃይል አምኖ በፈረሱና በበቅሎዎቹ ልጓም በጦር መሣሪያው በሠራዊቶቹ ልብስ ላይ እንዲሁም በሰንደቅ ዓላማው ላይ አስቀርጾ ቢገጥም መክስምያኖስና ሠራዊቶቹን ድል አድርጓቸዋል፡፡ ለብዙ ዘመናት ተከፋፍላ ትኖር የነበረችውን ሮምንም አንድ አደርጎ በመልካም አስተዳደር መርቷታል፡፡ እኛም የዚህ ዓለም ገዥ የሆነውን ጠላታችን ዲያብሎስ እና ሠራዊቱን በመስቀሉ ኃይል ድል እንድናደግ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
   ፫ኛ. ምልክታችን ወይንም መለያችን ነው፡-የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታታይ ኦርቶዶክሳዊ ምእመናን የሆነው ሁሉ ከሌላው እምነት የሚለየው በመስቀሉ ምልክትነት ነው፡፡መስቀል ለኛ ለተዋሕዶ ልጆች የማንነታችን መለያ የሕይወታችን አሻራ ነው፡፡ መስቀል መለያ ወይም ምልክት ይሆነን ዘንድ የሰጠን እግዚአብሔር ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ‹‹ከቀስት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው›› (መዝ ፶፱÷፬) በመስቀሉ ምልክትነት ከዓለም ሕዝብ የለየን ለአንድ ዓላማ የጠራን እግዚአብሔር ነው፡፡ የእርስዎ መለያ ምልክት ምንድን ነው? መስቀሉ ወይስ ሌላ?
    ፬ኛ. መስቀል ሰላማችን ነው፡– ሰላም ስምምነት አንድነት ኅብረት ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ሰላም የሰው ልጅ ወጥቶ ሊገባ አይችልም፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ሲፈጥረው በሰላም በስምምነት በአንድነት መኖር እንዲችል አድርጎ ነው፡፡ ይሁንም እንጂ የሰው ልጅ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱና ከእግዚአብሔር በመለየቱ ለ፭ ሺህ ፭፻ ዘመን ሰላሙን አጥቶ በመቅበዝበዝ ኑሯል፡፡ የሰው ልጆች መቅበዝበዝ ያለ ሰላም መኖር ያሳዘነው ጌታ ወደ ዚህ ዓለም መጥቶ የሰላምን ወንጌል አስተምሮ የተበተነውን ሕዝብ ሰብስቦ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የተነጠቁትን ሰላም ለአዳምና ለልጆቹ መለሰላቸው፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ‹‹በመስቀሉ ሰላምን አደረገ›› ሲል የዘመረው በመስቀሉ ሰላምን ኅብረትን አንድነትን ሕይወትን አግኝተናል በመሆኑም ቅዱስ መስቀል ለኛ ለተዋሕዶ ልጆች ሰላማችን ነው(ቆላ. ፬÷፲፱ ኤፌ.፪÷፲፫-፲፰)
፲፪.መስቀል ለምን እንሳለማለን ?
ሐዋርያዊት ጥንታዊት፣ ዓለም ዓቀፋዊት ኵላዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ደመ ወልደ እግዚአብሔር የፈሰሰበትን ሥጋ ወደሙ የተፈተተበትን ከዲያብሎስ ወጥመድ አምልጠን ነጻ የወጣንበት ከባዱን የዲያብሎስን ሸክም ያቀለልንበት ቅዱስ መስቀልን አክብረን እንድንሳለመው ዘወትር ታስተምራለች፡፡ የተወዳዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን የተቀደሰውን ነገር አክብረን ብንሳለመው ብንዳስሰው በረከት እንደምናገኝና እንደምንቀደስ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡ ‹‹ሁሉንም ትቀድሳችዋለህ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱሳን ይሁናሉ›› (ዘፀ.፴÷፳፱) በማለት ያስረዳል፡፡ እኛም በቅዱስ መስቀሉ ላይ አድሮ እግዚአብሔር እንደሚቀደሰንና እንደሚባርከን አምነን እንሳለመዋለን፡፡ በአጠቃላይ መስቀል የምንሳለመው ስለ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች ነው፡-
፩. ሥርየተ ኃጢአትን ለመቀበል፣
፪. መንፈሳዊ ክብርንና ፀጋን ለመቀበል፣
፫. ለመስቀሉ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ ስንል መስቀል እንሳለማለን፡፡

፲፫.በመስቀል መባረክ ወይም መሳለም የተጀመረው መቼ ነው?
በመስቀል አምሳል መባረክ ወይንም መሳለም የተጀመረው በዘመነ ኦሪት ወይም በብሉይ ኪዳን ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ሙሴናእና ካህኑ አሮን ይባርኩ እንደነበረና እግዚአብሔርም ቡራኬያቸውን ተቀብሎ ሕዝቡን በማያልቅበት በረከት ይባርክ እንደ ነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ ‹‹ስትባርካቸውም እንዲህ በላቸው እግዚአብሔር ይባርክህ ይጠብቅህም—–እኔምእባርካቸኋለሁ›› ‹‹አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም››(ዘሌ.፱÷፳፪) ይላል፡፡ኦሪትን ሊሽር ሳይሆን ሊያጸናት የመጣ ፈጻሜ ሕግ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ደቀ መዛሙርቱን ሲባርካቸውም በኋላ ወደ ዓለም ለወንጌል አገልግሎት እንደላካቸው ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ ‹‹እስከ ቢታንያም አወጣቸው እጁንም አንሥቶ ባረካቸው››(ሉቃ.፳፬÷፶) አባቶቻችን ካህናትም እግዚአብሔር ለሙሴ እና ለአሮን የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩ እንዲህ በሏቸው በተባሉት የቡራኬ ቃል መሠረት ይባርኩናል በረከትንም እንቀበላለን፡፡
     ፲፬. በዓለ ቅዱስ መስቀል
ክርስቶስ በወርቀ ደሙ የዋጃት ቤተክርስቲያን ምእመናን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን እንዲያገኙ ከአምላካቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲኖሩ ለቅዱሳን ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት እንዲገልጹ በዓላትን ሰፍራ ቆጥራ ይዛ በየወሩና በየዓመቱ መታሰቢያቸውን በላቀና በደመቀ ሁኔታ ታከብራለች፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱና ዋነኛው ክርስቶስ ተሰቅሎ ፍቅሩን ለዓለም ሕዝብ የገለጠበት የከበረ ሥጋውንና ደሙን ለልጆቹ ያደለበት መስከረም ፲፯ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የመስቀል በዓል ተጠቃሽ ነው፡፡
ሀገሯ ሀገረ እግዚአብሔር ሕዝቧ ሕዝበ እግዚአብሔር ምድሯ ምዕራፈ ቅዱሳን በሆነችው በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በሊቃውንቱ ያሬዳዊ ዝማሬ በእናቶች ዕልልታ በወጣቶች ሆታ በሰንበት ትምህርት ቤቶች ዝማሬ ተውበውና ደምቀው ከሚከበሩ መንፈሳዊና ዓመታዊ በዓላት መካከል አንዱ በዓለ ቅዱስ መስቀል ነው፡፡
ይህን መንፈሳዊ በዓል ለማክበር ኦርቶዶክሳውያን እንደ ሰማያውን መላእክት ነጫጭ ልብሶችን ለብሰው በልብሳቸውም መስቀሉን አስጠልፈው ለቅዱስ መስቀል ያላቸውን ፍጹም የሆነ ፍቅር ይገልጻሉ፡፡ ይህን በዓል ለማክበር ነገሥታት ከዙፋናቸው ጳጳሳት ከመንበራቸው መነኮሳት ከገዳማቸው መምህራን ደቀመዛሙርት ከጉባኤ ቤቶቻቸው ካህናት ዲያቆናት ምእመናን በአንድነት በአራቱም መዓዝናት ወጥተው እንደ ቅድስት ዕሌኒ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምነውና ታምነው በመስቀሉ ፍቅር ተማርከው በፍጹም ደስታ በየዓመቱ በአደባበይ ያከብሩታል፡፡
ምእመናን ይህን በዓል ሲያከብሩ በዓይነ ሕሊና የመስቀሉን ቅርጽ ብቻ ሳይሆን በመስቀል ላይ ለሰው ልጆች ሲል በችንካር የተቸነከረ ደሙን ያፈሰሰ የክርስቶስን ውለታ በዓይነ ሕሊና ስለው በአዕምሯቸው ቀርጸው በልቡናቸው አንግሠው አንደበታቸውን በዝማሬ ያከብሩታል፡፡ ቅዱስ መስቀል በኢትዮጵያ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ይታሰባል፡፡ ምንም እንኳ መስቀል የሌለበት ቤተ ክርስቲያን ባይኖርም በተለይ በቅዱስ መስቀል ስም በታነፁት አብያተ ክርስቲያናት ዘወትር ክብረ መስቀል ይነገራል፡፡
ከዘጠኙ የጌታችን ንዑሳን በዓላትም አንዱ ቅዱስ መስቀል ነው፡፡ይሄውም በየዓመቱ መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት ከ፪፻ ዓመት በላይ ተቀበሮ ከኖረ በኋላ ተቆፍሮ የወጣበትን ምክንያት በማድረግ በከተማም ይኹን በገጠር በላቀና በደመቀ ሁኔታ ይከበራል፡፡ግማደ መስቀሉ በተቀመጠበትም በግሸን ደብረ ከርቤ መስከረም ፳፩ ቀን ብዙ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች በተገኙበት ይከበራል፡፡ እኛም መስቀሉን አክብረን በመስቀሉ ኃይል አምነን ዲያብሎስን ድል ነሥተን ስለእኛ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሞተውን ክርስቶስን አምልከን በተዋሕዶ ሃይማኖት ጸንተን የመንግሥተ ስማያት ዜጎች እንድንሆን እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡ወለወላዲቱ ድንግል፡ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡