ፈተና

 መጋቤ ምሥጢር ቀሲስ ስንታየሁ አባተ (አውስትራልያ)

                    ክፍል  አንድ

ፈተና በሕይወት ዘመናችን በቤተ ክርስቲያናችን እምነት ሥርዓት ቀኖናና ትውፊት መሠረት በምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞና እንቅስቃሴ ውስጥ ያለ ጥፋታችን ከተለያዩ አካላት የሚገጥመን መሰናክል እንቅፋት መከራ ስደት ወይም በሂደት ሊጎዳንና ሊያሰናክለን የሚችል አሁን ግን መልካም መስሎ የሚታየን ነገር ሊሆን ይችላል። በቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ መሠረት ፈተና ከሦስት ታላላቅ ምንጮች ሊመጣብን ይችላል።

  1. ከራሳችን

በተለያዩ የስሜት ሕዋሳቶቻችን በኩል ወደ ልባችን የሚገቡና እንደ እግዚአብሔር  ፈቃድ ያልኾኑ ወይም በቅዱሳት መጻሕፍት ከተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ የተለዩ አሳቦች በሂደት ወደ ምኞት ያድጋሉ። በምኞት የሚጀምረው ፈተና በተግባር ሲፈጸም ደግሞ ኃጢአት ይሆናል። ይኽንን ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ”ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም። ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች” ብሏል  (ያዕ. ፩:፲፫-፲፭)

ጠቢቡ ሰሎሞንም በምሳሌው ” የሰው ስንፍና መንገዱን ታጣምምበታለች፥ ልቡም በእግዚአብሔር ላይ ይቈጣል” ብሎ በስንፍና የምንያዝበት የአሳብና የምኞት መንገዳችን በሂደት የሚያስከትለውን መዘዝ አስረድቷል። (ምሳ. ፲፱፥፫) ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገዛ የስሜት ሕዋሳቶቻችን ፈተና የሚያመጡብን መኾናቸውን ““ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል” ብሏል (ማቴ.፲፥፴፮ )

በዚህ መሠረት በአንደበታቸው የማይገባ ነገር ተናግረው: በዐይናቸው መጥፎ ነገር አይተው: በጆሯቸው ክፉ ምክርና ወሬ ሰምተው: በሐፀ ዝሙት ተነድፈው በእጃቸው ወንጀል ሠርተው በእግራቸውም የኃጢአት ወጥመድ ወደ ተጠመደበት ተራምደው ሄደው በነፍስ በሥጋ ታላቅ ጉዳት ላደረሰባቸው ፈተና የተዳረጉ ወገኖቻችን በርካቶች ናቸው።

  1. በዙርያችን ካለው ማኅበረሰብ

ሰው ማኅበራዊ ፍጡር ነው። ቅድስት ኦሪት “ለሰው ብቻውን መኖር አይገባም” እንዳለችው በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የምንኖረው ከሌሎች ጋር ነው። በምንኖርበት በምንሠራበት በምንጓዝበት በመሳሰሉት ኹሉ በእምነት በባህል በአመለካከት በዕድሜ በጾታና በመሳሰሉት ሁሉ ከተለያዩ ሕዝብ ጋር እንገናኛለን። በዚህ አብሮነት ደግሞ የእውቀት የልምድ የአመለካከት ልውውጥ ይከሰታል። ደካማው በብርቱዎቹ ተጽዕኖ ይደረግበታል። በደካማነቱ እምነታቸውን ባህላቸውን ክህደታቸውን ሥጋዊ ፈቃዳቸውን ይጭኑበታል። በዚህም ጌታችን በእሾህ መካከል የወደቀ ዘር ብሎ እንዳስተማረው መልካም ክርስትናውን ከግራ ከቀኝ ያስጨንቁበትና ያለ ፍሬ እንዲቀር ያደርጉታል።

የሔዋን ምክንያተ ስሕተት መኾን: ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ይኾናል። ቅዱስ ጳውሎስም “አትሳቱ፤ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” ያለው ፈተና በዙርያችን ካሉና ከፈቃደ እግዚአብሔር ካፈነገጡ ሰዎች ስለሚመጣ ነው። (፩ኛ ቆሮ.፲፭፥፴፫) ስለኾነም ነው ክቡር ዳዊት  “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” በማለት  ያስረዳው።(መዝ.፩፥፩ )

በክፉዎች ምክር የሚሄድ በኃጢአተኞች መንገድ (አሳብ ምክር) የሚሄድ በዋዘኞች ወንበር የሚቀመጥ (ድርጊት የሚተባበር) ለፈተና የተዳረገ ይኾናል። ይኸው ክቡር ዳዊት በሌላኛው መዝሙሩ ይኽንን አሳቡን ሰፋ አድርጎ “ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ” በማለት በዙርያችን ካሉት ሰዎች የተነሣ የሚገኘውን በረከትና የሚመጣብንን ፈተና አስረድቷል። (መዝ.፲፯:፳፭)

  1. ከሰይጣን

ሰይጣን ሥራው መፈታተን: ማዘግየት: ማሰናከልና መክሰስ ነው። ይኽ የማያቋርጥና ተስፋ የማይቆርጥ ባላጋራ ምእመናን በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዲክዱ አንድነታቸውን እንዲያፈርሱ ምግባር ትሩፋታቸውን እንዲተዉ ንጽህናቸውን እንዲያረክሱ በክፉ ድርጊት ፈጣሪያቸውን እንዲያስቆጡ ተስፋ እንዲቆርጡ ይፈታተናቸዋል። ምክንያቱም እርሱ ፈታኝና መፈታተንም ሥራው ስለኾነ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ የዚኽን ጨካኝ ባላጋራ መፈታተንን “በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት” እያለ አስተምሮናል።

ፈታኝ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን በክፉ ምክሩ ከገነት አስወጥቷል። ቃየል ወንድሙ አቤልን እንዲገድለው መግደልን አስተምሯል። በበለዓም አድሮ እስራኤል የሚጠፉበትን ለባላቅ አስመክሯል። በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ኢዮብን ከስሷል። በምናሴ አድሮ ነቢየ ልዑል ኢሳይያስን በመጋዝ አሰንጥቋል።በሄሮድስ አድሮ 144,000 ሕፃናትን አስፈጅቷል። ሕፃኑ ክርስቶስን ከእናቱ ጋር እንዲሰደዱ አድርጓል። ጌታችንን በገዳመ ቆሮንቶስ ፈትኗል። ትንሣኤውን በአይሁድ አድሮ አስክዷል። ሐዋርያትን አሳድዷል። አስገድሏል። ሰማዕታትን በአላውያን ነገሥታት አድሮ አስጨፍጭፏል። ቤተ ክርስቲያንን አሳድዷል። አሁን እያሳደዳት ይገኛል። ብዙዎችን በፈተናውና በመከራው ጽናትና ብዛት ተስፋ አስቆርጧል።

ሰይጣን ፈተናውን የሚያመጣው አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሰይጣንነቱን ገልጦ ጨለማ ፊቱን አሳይቶ ሳይሆን እጅግ በተለያዩና በረቀቁ ስልቶች ነው። በክፋት ብቻ ሳይሆን በፍቅር እየተመሰለ: ሃይማኖተኛና ለእምነት ተቆርቋሪ እያስመሰለ: በድካማችን ረዳት በረሃባችን ምግብ በብቸኝነታችን ወዳጅ በጭንቀታችን አረጋጊ በድህነታችን ብልጥግና ሆኖና መስሎ ነው የሚቀርበን። ይኽንንም ወደ ጌታችን ቀርቦ መራቡንም አይቶ “ይኽን ድንጋይ ዳቦ አድርገህ ብላ” ካለው መረዳት ይቻላል። (ማቴ.፬፥፬)

በክርስትና ስንኖር ወደድንም ጠላንም ፈተና ከሦስቱ መንገዶች ቢያንስ በአንዱ ወደ እኛ መምጣቱ አይቀርም። እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ክርስቲያን ኾኖ ያለ ፈተና መኖር ጨርሶ አይቻልም። ከሰው ርቀው በበረሓ ቢኖሩ: ከኃጢአት ተለይተው ቅድስናን ገንዘብ ቢያደርጉ: በዚኽ ዓለም ሀብትና ክብር ቢከበቡ: የመጨረሻውን የሥልጣን ቁንጮ ቢጨብጡ ያለ ፈተና መኖር አይቻልም።አለመቻሉንም ቅዱሳት መጻሕፍት ተባብረው አስረድተዋል። ጌታችን በቅዱስ ወንጌሉ “ወዮ ለዓለም፤ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና” ብሏል። ማቴዎስ 18፥7። በሌላኛው ወንጌሉም ““በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሎ አስረድቶናል።( ዮሐ.፲፮፥፴፫)

በክርስቶስ ለሐዋርያነት የተጠራና ከእርሱም የተማረው ቅዱስ ጴጥሮስ መከራና ፈተና የማይቀሩ በመኾናቸው “ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።

ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር” በማለት በስፋት የመከረን (፩ኛ ጴጥ.፬:፲፪-፲፮) ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ ፈተናና መከራ አንዱ የተጠራንለት መኾኑን “በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና” በማለት አስተምሮናል (ፊል.፩:፳፥-፴ )

ይኽንን እውነታ ያልተረዱ አንዳንድ ምእመናን ክርስቲያን በመኾናቸው ብቻ በራሳቸው: በቤተሰባቸው: በቤተ ክርስቲያን: በማኅበረ ምእመናን ላይ ፈተና መከራና ስደት ሲመጣ ይረበሻሉ። እግዚአብሔርን ለምን ብለው ይሞግታሉ። እምነታቸው ስሕተት ያለበት መስሎ ይታያቸዋል። በስም ክርስቲያን የተባሉና በዙርያቸው የሚኖሩ በዓለሙ ደልቷቸው የሚኖሩ “ክርስቲያን” የሚባሉ ሰዎች ያላቸውን ሰላም: የሚያገኙት በረከትና ስኬት እያዩ ክርስትናቸውን በምድራዊ በረከት መመዘን ይጀምራሉ።  በተለይ ደግሞ በዘመናችን እያየነው እንዳለነው የፈተናው ምንጭ የቤተ ክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች መኾናቸውን ሲያዩ እጅጉን በእምነታቸው የሚናወጹ አሉ። ይኽ ግን ክርስትናው ከዘመናችን ለመድረስ ያለፈበትን እጅግ ውጣ ውረድ የበዛበትን ጉዞ ካለመረዳት የሚመጣ ነው።የመጀመርያው የክርስትና ፈተና የመነጨው ከጌታችን እግር ተቀምጦ ይማር የአንደበቱን ቃል ይሰማ የእጁንም ተአምራት ያይ ከነበረው ከይሁዳ ነው።

ይቀጥላል !

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *